የ37 ዓመቱ ስፔናዊ ግብ ጠባቂ ኢከር ካሲያስ ወደ እናት ሀገሩ ስፔን ተወዳጅ የሊግ ውድድር (ላ ሊጋ ሳንታንዴር) ተመልሶ የመጫወት እና በአምበልነት ባገለገለበት ብሔራዊ ቡድንም ዳግም የመጠራት ህልም እንዳለው ተናግሯል፡፡
የቀድሞ የሪያል ማድሪድ ጀግና ተጫዋች ቃል በቃል እንዳለው በላ ሊጋው በድጋሜ መጫወት ቢችል እንደሚወድ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
በማድሪድ ከወጣትነቱ ጀምሮ ያደገው ግብ ጠባቂ ስኬታማ 16 ዓመታትን ከዋና ከተማው ቡድን ጋር ያሳለፈ ሲሆን አምስት የላ ሊጋ እና አራት የቻምፒዮንስ ሊግ ድሎችን አሳክቶ በ2015 ነበር ወደ ፖርቱጋሉ ቡድን ፖርቶ የተጓዘው፡፡
አንጋፋው ግብ ጠባቂ ከፖርቱጋሉ ቡድን ጋር ያለው ውል በተያዘው የውድድር ዓት ማብቂያ የሚጠናቀቅ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በፖርቶ የሚያቆየውን ስምምነት ሊፈፅም እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ቢሆንም ግን ወደ ሀገሩ ተመልሶ ከዚህ በፊት በሀገሩ ሊግ የከወናቸውን የ510 የጨዋታ መጠን ላይ የመጨመር ህልም እንዳለው ተነግሯል፡፡
‹‹ በላ ሊጋው በመጫወቴ እንደ እድለኛነት አየዋለሁ፤ አሁን ግን እዛ አይደለሁም›› ሲል ተናግሯል፡፡
በማድሪድ ያሳለፍኩትን ህይወት እንደገና ማግኘት ከባድ ነው የሚለው ካሲያስ፤ እነዛን ድሎች በድጋሜ ማሳካት በጣም አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
‹‹ በማድሪድ የነበረኝ ጊዜ ያለፈ ታሪክ ነው፤ ብቻ ግን ወደ ላ ሊጋው መመለስን እሻለሁ ›› ሲልም ይናገራል፡፡
ከስፔን ብሄራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫን እና የአውሮፓ ዋንጫዎችን ያነሳው ኢከር ካሲያስ ለሀገሩ አገልግሎት ከሰጠ ሶስት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ የላ ሮሃዎቹ ስኬታማ ስብስብ አባዛኛዎቹ ተሰላፊዎች የብሔራዊ ቡድን ግዴታቸውን እያጠናቀቁ ባሉበት ጊዜ ፤ እርሱ ግን ከስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሊዩስ ኢነርኬ ጥሪን ይናፍቃል፡፡
እርሱም የብሔራዊ ቡድን ጉዞዬ አልተጠናቀቀም፤ እንደሌሎቹም ተጫዋቾች ከቡድኑ ራሴን አላገለልኩም ብሏል፡፡
ሀሳቡን ሲያጠናክርም ‹‹ ሲመስለኝ ልዩነቱ የግብ ጠባቂዎች ነው፤ ቢሆንም አሰልጣኙ ያመነበትን ውሳኔ አከብራለሁ፣ ምክንያቱም እነርሱ የተሻሉ ናቸው ብሎ ስለሚያስብ ነው›› ሲል ጨምሯል፡፡
በስፔን ብሔራዊ ቡድን አሁን ላይ የማንችስተር ዩናይትዱን ግብ ጠባቂ ዳቪድ ዴ ሂያ፣ የቼልሲውን ኬፓ አሪዛባላጋ እና የናፖሊው ፔፔ ሬና እንዲሁም የሪያል ቤቲሱን ፓው ሎፔዝ ተመራጭ ናቸው፡፡
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን ከተመለከተቻቸው እና ካጨበጨበችላቸው ግብ ጠባቂዎች አንዱ የሆነው አንጋፋው ኢከር ካሲያስ ወደ ስፔን መመለስን፤ በላ ራሆዎቹ ስብስብ ዳግም መጫወትን አሁንም ግን አጥብቆ ይሻል፡፡
ጎል ዶት ኮም