የዋሊያ ቢራ አክሲዮን ማህበር ለአራት ዓመታት የሚዘልቅ የ56 ሚሊዬን ብር የስፖንሰርሽፕ (አጋርነት) ስምምነት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ፈፅሟል፡፡
ስምምነቱ በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ እና በሃይንከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዩጂን ዩባሊጆሮ መካከል በካፒታል ሆቴል ሲከናወን፤ በየዓመቱ 14 ሚሊዬን ብር ታሳቢ የሚሆን በወንዶች ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) እና ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ላይ ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል፡፡
ዋሊያ ቢራ ከዚህ ቀደም ለአራት አመታት የወንዶች ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ብቻ ዋና አጋር የነበረ ሲሆን አሁን ሁለቱም ዋና ብሔራዊ ቡድኖች በስምምነቱ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
ስምምነቱ ምግብና መጠቶች ላይ አስመልክቶ የወጣውን አዲስ አዋጅ መሰረት አድርጎ እንደተፈፀመም በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ተነግሯል፡፡
አዲሱ የአራት ዓመት ስምምነት ከጥር 1/2019 እስከ ታህሳስ 30/2022 ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡