ህብረቱ ለኢትዮጵያ ያለውን አድናቆት ገለፀ ፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት አዋጅን በማፅደቋ ምስጋና ይገባታል አለ፡፡
በህብረቱ የንግድ እና ኢንዱስትሬ ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ በቱይተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ የኢትዮጵያን ውሳኔ ወቅታዊ እና ታሪካዊ በማለት አሞካሽተውታል፡፡
ሙቻንጋ ከኢትዮጵያ ፓርላማ ይሄን ውሳኔ መስማት ለህብረቱ ትልቅ እና መልካም ዜና ነው፤ ከእንግዲህ አንድ የአፍሪካ ሀገር ብቻ ስምምነቱን የሀገሩ ህግ አድርጎ ቢያፀድቅ ስራችንን በፍጥነት እንጀምራለን ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመመስረት እንዲችል ቢያንስ 22 ሀገራት ስምምነቱን የራሳቸው ሀገር የህግ አካል አድርገው ማፀደቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ 21ኛ ሀገር ሆና ስትፈርም ህብረቱ የወጠነውን ዓለማ ለማሳካት ጫፍ ላይ መድረሱን የሚያመለክት መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2022 በአህጉሪቱ የሚኖረውን የእርስበርስ የንግድ ልውውጥ በ52 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡
አፍሪካዊያን በዚህ የንግድ እንቅስቃሴ ሲሳተፉ 90 በመቶ የሚሆነው በሸቀጦች ላይ የሚጣለው ታሪፍ የሚነሳላቸው ሲሆን በአገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያሉ እንቅፋቶችንም ያስወግድላቸዋል፡፡
አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው ይህ ቀጠናዊ ነፃ የንግድ ስምምነት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣር በ1995 ዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ከተመሰረተ ወዲህ የተቋቋመ ትልቁ የንግድ ቀጠና ነው፡፡
ስምምነቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ አመታዊ ሀገራዊ ጥቅል ምርታቸው ከ3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ በሚገመት 1.2 ቢሊዮን ደንበኞች መካከል የንግድ ትስስርን ይፈጥራል፡፡
መንገሻ ዓለሙ