ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን ብሔራዊ ቡድኖች የምድብ የመጨረሻ ጨዋታቸውን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት አድርገው፤ በውድድሩ ተካፋይ የሚሆኑ ብሔራዊ ቡድኖች በሙሉ ተለይተው ታውቀዋል፡፡
ካፍ የውድድሩን አዘጋጅነት ከካሜሮን ነጥቆ ለግብፅ አሳልፎ መስጠቱ ይታወሳል፤ በ12 ምድቦች ተከፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን ሲያካሂዱ ከነበሩ ቡድኖች መካከል አስቀድመው የተቀላቀሉ ቡድኖችን ጨምሮ 24ቱ ተለይተው ታውቀዋል፡፡
በእኛ ክረምት ለመጀመሪያ ጊዜ በ24 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል በሚካሄደው ውድድር፤ ከአሁን በኋላ የምድብ ድልድል እና ጨዋታው የሚጀመርበት ቀን ብቻ ይጠበቃል፡፡
በዚህም ምድብ D ላይ ቤኒን ቶጎን 2 ለ 1 ስትረታ፤ ቅዳሜ አልጀሪያ ከጋምቢያ በ1 ለ 1 አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ አልጀሪያ እና ቤኒን ደግሞ ተያይዘው ማለፍ ችለዋል፡፡
ምድብ E ተጠባቂ በነበረው ጨወታ ደቡብ አፍሪካ በትናንትናው ዕለት ሊቢያን 2 ለ 1 ረትታ የውድድሩ ተካፋይነቷን አረጋግጣለች፡፡ ከምድቡ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የውድድሩን ትኬታቸውን ለመቁረጣቸው እርግጠኛ ሁነዋል፡፡
በምድብ G ዲ.ሪ. ኮንጎ 1 ለ 0 ላይቤሪያ፤ ዚምባብዌ 2 ለ 0 ኮንጎ ሲረቱ ዚምባብዌ እና ዲ.ሪ ኮንጎ ከምድቡ ቀዳሚ ሁነው አልፈዋል፡፡
ምድብ H ላይ ደግሞ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ከጊኒ ጋር ያለግብ በአቻ ውጤት ሲለያዩ፤ አይቮሪ ኮስት ሩዋንዳን 3 ለ 0 ድል አድርጓል፡፡ ጊኒ እና አይቮሪ ኮስት ወደ ውድድሩ መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ምድብ L ኬፕ ቨርዴ 0 ለ 0 ፣ ታንዛኒያ 3 ለ 0 ዩጋንዳ በሆነ ውጤት ሲለያዩ ፤ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ ማጣሪያውን የተሻገሩ ቡድኖች ናቸው፡፡
በሌሎች ምድቦች ጨዋታዎች፤ ምድብ A ላይ ሴኔጋል እና ማዳጋስካር፤ ከምደብ B ሞሮኮ እና ካሜሮን፤ ከምድብ C ማሊ እና ቡሩንዲ፤ ከምድብ F ጋና እና ኬንያ፤ ከምድብ I አንጎላ እና ሞሪታኒያ ፤ ከምድብ J ቱኒዚያ እና ግብፅ እንዲሁም ከምድብ K ጊኒ ቢሳው እና ናሚቢያ በአፍሪካ ዋንጫ ተካፋይ ሀገራት ናቸው፡፡