የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጎላን ኮረብታዎች የእስራኤል ግዛቶች ናቸው ማለታቸው በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡
አሜሪካ የጎላን ኮረብታዎች የእስራኤል ሉዓላዊ ግዛት መሆናቸውን እውቅና መስጠቷን ተከትሎ በርካታ ሀገራትና እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተቃውሟቸውን እየገለጹ ይገኛል፡፡
ሶሪያ ከጅምሩ የትራምፕን ውሳኔ ሆን ተብሎ ሉዓላዊ ድንበሬን የሚጋፋ ጥቃት ነው ስትል ኮንናዋለች፡፡ ይዞታዎቹን ለማስመለስም ጥረት ማድረጓን እንደምትገፋበት አስታውቃለች፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አል ሙአለም አሜሪካ የጎላን ኮረብታዎች የእስራኤል አካል ናቸው የሚል ይፋ እውቅና መስጠቷ ሌላውን ወገን ያገለለ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም ምንም ያህል በውዝግብ አመታት ቢቆጠሩም የጎላን ኮረብታዎች የሶሪያ ግዛት የመሆናቸውን እውነታ አይቀይረውም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የፍልስጤሙ ፕሬዜዳንት ማህሙድ አባስ እንዲሁም ጋዛ የሚገኘው ሃማስ ታጣቂ ቡድን የአሜሪካንን ውሳኔ በጽኑ ከተቃወሙት መካከል ናቸው፡፡
ማህሙድ አባስ በመግለጫቸው የአሜሪካ እውቅና መስጠት የተባበሩት መንግስታትን ውሳኔ የሚያስቀይር ምንም አይነት የህግ ማዕቀፍ እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡
የሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ የጎላን ኮረብታዎች እስከወዲያኛው የሶሪያ ግዛት እደሆኑ ይቀጥላሉ ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፈን ዱጃሪክ የጎላን ኮረብታዎችን በተመለከተ ምንም የውሳኔ ለውጥ አለመደረጉን ነው የተናገሩት፡፡
እንደ አልጄዚራ ዘገባ የአሜሪካ ውሳኔ ከኔቶ እና ከአረብ ሊግ ከፍተኛ ተቃዎሞ የገጠመው ሲሆን በጎላን ኮረብታዎች እጣ ላይም የሚቀይረው ነገር አለመኖሩም እየተነገረ ነዉ ፡፡
በአብነት ታምራት