የቦይንግ ኩባንያ በአዳዲሶቹ የቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላኖች ላይ አዲስ የሶፍትዌር ስርአት እና የፓይለቶች ማሰልጠኛ መመሪያ ይፋ አድርጌአለሁ ቢልም የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግን ለዚህ ስልጠና ፓይለቶቹን የመላክ እቅድ እንደሌለው እየተናገረ ነው።
አለም አቀፍ የአቪዬሽን ኤክስፐርቶች አዳዲሶቹ የአውሮፕላን ስሪቶች ላይ አንዳች የሶፍትዌር ችግር እንዳለ ሁለቱም አደጋዎች ፍንጭ ይሰጣሉ ካሉ በኋላ ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡
የኢንዶኒዢያው ላየን አየር መንገድ አውሮፕላን በተከሰከሰ በአምስተኛ ወሩ የኢትዯጵያ አየር መንገዱ አደጋ ሲደገም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ የሚባሉ አየር መንገዶች የ737 ማክስ ኤት አውሮፕላን ስሪቶችን ከበረራ ለማገድ ወሰኑ፡፡
ይህ ደግሞ በግዙፉ የ አሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ላይ የቢሊዮን ዶላሮች ኪሳራን እና ለዘመናት የገነባውን ዝናውንም ጭምር እንዳሳጣው ሲነገር ቆይቷል፡፡
የጨነቀው እንዲሉ አጣብቂኝ ውስጥ ያለው ቦይንግ ለተከሰቱት ሁለት የመከስከስ አደጋዎች ዋናው የችግሩ ምንጭ እንደሆነ አለም አቀፍ የአቬሽን ኤክስፐርቶች የጠቆሙትን “ኤምካስ” የተሰኘውን የመቆጣጠሪያሶፍትዌር ሲስተም ነው አሁን ቀይሬያለሁ ያለው፡፡
ቦይንግ ይህን ይፋ ያድርግ እንጂ እንዳይበሩ የተደረጉት የብዙ አገራት የማክስ ኤት ስሪት አውሮፕላኖቹ በቅርቡ ወደ ሥራ ይመለሳሉ የሚል ግምት ግን የለም።
የዚህን ምክንያት የሚገልጹት የሲኤንኤን የአቬሽን ተንታኞች እንደሚናገሩት ብዙ አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የተከሰከሰበት ምክንያት በግልፅ የሚያሳይ ውጤት በምርመራ ላይ ካለው የመረጃ መመዝገቢያ ሳጥን እየጠበቁ በመሆኑ ነው ይላሉ።
ይህን ኤምካስ የተባለውን የበረራ መቆጣጠሪያ ስርዓት አድሸዋለሁ የሚለው ቦይንግ አዲሱ ሶፍትዌር አውሮፕላኖቹ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ቢገቡ ማስጠንቀቂያ የሚልክ ዘዴ እንዳለው ገልፃል፡፡
ቦይንግ እንደሚለው ይህ አሁን ተሻሽሎ ይገጠማል የሚባለው የቅድመ ጥንቃቄ ሰጪ ሶፍትዌር ሲስተም በኢንዶኒዢያውም ሆነ በኢትዮጵያው አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ እንዳልነበረ እና ሲስተሙ መገጠሙ አውሮፕላኑ ሰላማዊ በረራውን የሚቃረኑ ምልክቶችን ሲሰጥ ስርዓቱ ለፓይለቶቹ ጥቆማን መስጠት የሚያስችል ነው፡፡
የሟች ቤተሰቦች የአደጋውን ሪፖርት በመጠባበቅ ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት ቦይንግ ለደንበኞቹ ይህን ሲስተም የምገጥምላችሁ በነጻ ነው፤ አንዳችም ክፍያ አልጠይቃችሁም ማለቱ በአየርመንገዶች እና በደንበኞቻቸው ላይ እያፌዘ ነው አስብሎታል።
አልጀዚራ እንዳስነበበው በአዲስ መልክ አዘጋጀሁ ያለው የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ማንዋል ላይ ዋሽንግተን ወደሚገኘው መስሪያ ቤቱ ከ200 በላይ አብራሪዎችን ለስልጠና ጋብዟል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን አብራሪዎቹን ለዚህ ስልጠና ለመላክ እቅድ እንደሌለው በኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሸን ዳይሬክተሩ አቶ አስራት በጋሻው በኩል ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።
እንደአቪዬሽን ኤክስፐርቶች ማብራሪያ ተሻሻለ የተባለው የሶፍትዌር ስርዓት ኤምካስ በሚባል ምህጻረ ቃል የሚታወቅ ሲሆን ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም ተብሎ ይተነተናል፡፡
ሲስተሙ አውሮፕላኑ የሞተሩን ክብደት እና ሞተሩ የተቀመጠበትን ቦታ ምክንያት አድርጎ በረራውን እንዳያቆም ያደርገዋል። ይህም አውሮፕላኑ ሽቅብ በሚወጣ ጊዜ ሚዛኑን እንዲያስጠብቀው ለማድረግ የተሰራ ነበር።
ቢቢሲ እንደዘገበው የኢንዶኒዢያው ላየን አውሮፕላን ምርመራ ውጤት ግን ይህ ሲስተም አውሮፕላኑ በአፍጢሙ እንዲደፋ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚልከው መልዕክት (ሲግናል) እርስበርሱ የሚጣረስ በመሆኑ ነው።
ይህ ደግሞ ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ነገር ነው። የተከሰከሰው የኢንዶኒዢያ አየር መንገድ ከ20 ጊዜ በላይ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል እንዲያዘነብል እንዲምዘገዘግ አድርጎታል ነው የተባለው።
በመሆኑም አሁን ቦይንግ አድሼዋለሁ የሚለው ሶፍትዌር በአውሮፕላኑ አፍንጫ የምትገኘው ሴንሰር እርስበርሱ የማይጣጣም መልእክት ካስተላለፈ ኤምካስ የተሰኘው መቆጣጠሪያ እራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
ቦይንግ ያመረታቸው የማክስ ኤት አውሮፕላን ስሪቶች እንዲህ ዓይነት መሠረታዊ እክል እያለባቸው እንዴት በተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ የይለፍ ፍቃድ አገኙ የሚለው ጉዳይ ግን ዓለምን እያነጋገረ ቆይቷል።
የሀገሪቱ የአቪየሽን ባለሥልጣን ተጠባባቂ ኃላፊ ዳንኤል ኤልወል በጉዳዩ ዙሪያ በአሜሪካ የሴኔት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ፊት ማብራሪያ እንዲሰጡ ለጥያቄ በቀረቡበት ወቅት ትልቅ ወቀሳ ደርሶባቸው እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል ፡፡
እንደውም ሴናተር ሪቻርድ ብሉሜንተል ባለስልጣን መስሪያቤቱ እራሱ መመርመር የነበረበትን ለቦይንግ ኩባንያ መስጠቱ “ቀበሮ የአውራዶሮ ማደሪያ ቆጥ እንዲጠብቅ” ከማድረግ የማይተናነስ ነው ሲሉ ተችተውታል።
የአሜሪካ ፌደራል አቪየሽን ባለሥልጣን በኢንዶኒዢያው እና በኢትዮጵያው አየር መንገድ አደጋዎች መካከል መመሳሰል እንዳለ ማመን ባይፈልግም መመሳሰሉን እንዲቀበል ግን ሳይገደድ አይቀርም፡፡
በዚሁ ጉዳይ ባለስልጣን መስሪያቤቱ ሊከሰስ እንደሚችልም እየተነገረ ነው፡፡