ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአራት አመት ጊዜ ይጠናቀቃል ፡፡
የግንባታው የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአራት አመት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሏል ፡፡
የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ መላውን የሀገሪቱን ህዝቦች በጋራ ማንቀሳቀስ የቻለ ፕሮጀክት ነው፡፡
አሁን ላይ የግድቡ የሲቪል ስራ 85 በመቶ ፣የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ 25 በመቶ እና የብረታብረት ስራ 13 በመቶ ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ፕሮጀክቱ 66 በመቶ ላይ ደርሷል ተብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከግድቡ ግንባታ መዘግየት እና ተያያዥ ችግሮች ምክኒያት የህዝባዊ ተሳትፎ መቀዛቀዝ አሳይቷል ፡፡
በመጀመርያው የግንባታ ጅማሮ ወቅት ትልቅ ሸለቆ በመገኘቱ ግንባታውን በሦስት ዓመታት ማራዘሙ፣ ሜቴክ የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የብረታ ብረት ሥራዎች ላይ ባደረገው ማሻሻያ ምክንያት የኮንትራት ማሻሻያ መደረጉ፣ የተጣበበ የኮንትራት ጊዜና የሜቴክ ሥራዎች መዘግየት እንደ ችግር ይነሳሉ፡፡
በመሆኑም ከሜቴክ ጋር የነበረው የሥራ ውል እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን ፣ ከሜቴክ ጋር በንዑስ ተቋራጭነት ሲሠሩ የነበሩ ተቋራጮችን ሙሉ የኮንትራት ማሻሻያ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡና አዳዲስ አምስት ተቋራጮች ቅድመ ክፍያ በመፈጸም ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
መንግስት የህዝባዊ ተሳትፎውን እንደገና ለማስጀመር እና ግድቡን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑ ተናግሯል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 8ኛ ዓመት በጉባ በመከበር ላይ ይገኛል።
የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 8ኛ ዓመት የግድቡ ግንባታ እየተካሄደ ባለበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ነው በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በመከበር ላይ የሚገኘው።
በክብረ በዓሉ ላይም የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብረሃም በላይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።