የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የመጀመሪያ ደረጃ የአደጋ ሪፖርት ዛሬ ይፋ ይደረጋል ተባለ
የትራንስፖርት ሚንስቴር ትናንት አመሻሽ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አደጋው ከደረሰበት በመጀመሪያዎቹ 30 ቀናት ውስጥ ቅድመ ሪፖርት እንዲቀርብ በሚጠይቀው መሠረት የምርመራው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ዛሬ ይፋ ይደረጋል፡፡
የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 ካፒቴኖች ቦይንግ ኩባንያ ያስቀመጣቸውን የአደጋ ጊዜ ርምጃዎች ቢወስዱም አውሮፕላኑን ግን መቆጣጠር እንዳልቻሉ ወል ስትሪት ጆርናል ትላንት አስነብቧል፡፡
ጋዜጣው በምርመራ ሂደቱ ውስጥ ያሉ ምንጮችን ጠቅሶ እንዳስነበበው ካፒቴኖቹ ችግሩ እንዳጋጠማቸው ወዲያውኑ MCAS የተሰኘውን ሶፍትዌር አጥፍተውት ነበር፡፡ ሆኖም መፍትሄ ሲያጡ ሶፍተዌሩን መልሶ እንዲሰራ አድርገው ሌሎች ዘዴዎችን ለመጠቀም ቢሞክሩም አደጋውን ግን ማስቀረት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
አውሮፕላኑ ፍጥነት የመቀነስ ምልክት ሲያሳይ አፍንጫውን ቁልቁል እንዲዘቀዘቅ በማድረግ እንዲከሰከስ ያደርገው ይሄው ሶፍትዌር እንደሆነ ይታመናል፡፡
ለዚህ መልስ የሚሰጠው የአደጋ ምርመራ ውጤት ዛሬ ይፋ ይደረጋል፡፡