የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሀግብር መቋጫ ግጥሚያ ዛሬ አመሻሹን 11፡ 00 ሲል በኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ መካከል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከናወናል።
ጨዋታው በሳምንቱ ከተካሄዱ መርሀግብሮች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ከሊጉ መሪ ክለቦች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ፤ ፋሲል ከነማ ደግሞ የሊጉ ዋንጫ ተፎካካሪነት ላይ ያለውን ጫና ለማበርታት ብርቱ ትግል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቡና ድል የሚያደርግ ከሆነ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተያዘውን የአራተኛነት ደረጃ በ31 ነጥብ መንጠቅ ያስችለዋል፤ የጎንደሩ ቡድን ደግሞ አሸናፊ የሚሆን ከሆነ በ35 ነጥብ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ይመለሳል፡፡
ጨዋታውን ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ እንዲመሩ ተመድበዋል።
ከዕለተ ዓርብ ጀምሮ በተካሄደው የ19ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀግብር ፤ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስን 1 ለ 0 ሲረታ ፤ ቅዳሜ ዕለት ሀዋሳ እና ባህር ዳር ከነማ በ1 ለ 1 አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
በትናንትናው ዕለት አምስት ግጥሚያዎች ሲከናወኑ፤ የሊጉ አናት ላይ የተሰየመው መቐለ 70 እንደርታ ትግራይ ላይ ወላይታ ድቻን 1 ለ 0 በማሸነፍ ያለውን ነጥብ 42 ሲያደርስ፤ ሲዳማ ቡና በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም አዳማ ከተማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 ውጤት በማሸነፍ የሰበሰበውን የነጥብ መጠን ወደ 34 አሳድጓል፡፡
ሽረ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ስሑል ሽረ ያለግብ በአቻ ውጤት ሲለያይ፤ ደደቢት አዲስ አበባ ላይ መከላከያን 2 ለ 1 ድል አድርጓል፡፡