በምስራቅ አፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀዉና በሩዋንዳ ኪጋሊ አስተናጋጅነት በ5 የስፖርት አይነቶች ማለትም በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ቴኳንዶ፣ የዉሃ ዳር መረብ ኳስ እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች ከመጋቢት 24 እስከ 28 በሩዋንዳ በተካሄደው፤ የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች የዞን 5 ሀገሮች የወጣቶች ጨዋታ በአትሌቲክስ ስፖርት ተሳትፎ ትልቅ ውጤት ይዞ የተመለሰው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ወጣት አትሌቶች ልኡክ፤ የእውቅና እና ሽልማት ስነ ስርዓት በኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተደርጎለታል፡፡
በውድድሩ የቀጠናው 11 ሀገሮች እና ፈረንሳይ በተጋባዥነት፤ በአጠቃላይ 12 ሀገሮች ጋር የተፎካከሩት 7 የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ልዑክ በውድድሩ ፍፃሜ ፤ ሁሉም አትሌቶች ሜዳሊያ በማምጣት 4 የወርቅ፣ 2 የብር እና 1 የነሀስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
የወርቅ ሜዳሊያዎቹን በ800ሜ ሴቶች በአትሌት ፍሬዘዉድ ተስፋዬ፣ በ1500ሜ ሴቶች በአትሌት መልካም አለማየሁ፣ በ1500ሜ ወንድ በአትሌት መልካሙ ዘገየ፣ በ3000ሜ ወንድ በአትሌት መንግስቱ በቀለ ፤ የብር ሜዳሊያዎቹ ደግሞ በ800ሜ ወንድ በአትሌት ጣሰዉ ያዳ፣ በ3000 ሜ ሴቶች በአትሌት መስዋት አማረ እንዲሁም የነሀስ ሜዳሊያ በ5000ሜ ወንድ በአትሌት ቦኪ ዲሪባ አማካኝነት ተገኝተዋል፡፡
የእውቅና እና ሽልማት ስነ ስርዓቱ በኢትዮጵያ ሆቴል ሲካሄድ ፤ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ወርቅ ላመጡ አትሌቶች እና ዋና አሰልጣኝ አቶ ሺሰማ ግርማ የ25 ሺ ብር ፤ ብር ላሳኩ 20 ሺ ብር ፤ ለነሀስ ደግሞ 15 ሺ ብር ሲሸልም ፤ ለቡድን መሪው አቶ ተፈሪ አላምረው የ30 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል ደግሞ በተሰጠ ሽልማት፤ ለቡድን መሪ እና ዋና አሰልጣኝ ለእያንዳንዳቸው 10 ሺ ብር ሲሰጥ፤ ለአትሌቶች ወርቅ ላጠለቁ 10 ሺ፣ ብር ላመጡ 7 ሺ እንዲሁም ነሀስ 5 ሺ ብር ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዝግጅቱ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው፤ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተ/ም/ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች አትሌቶች ባሳኩት ድል መደሰታቸውን ገልፀው በቀጣይም በአፍሪካ ጨዋታዎች እና በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በድል እንዲደምቁ በርትተው መስራት እንዳለባቸው አደራ ብለዋል፡፡