የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመጋቢት ወር 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 84 ሺህ ቶን የግብርና ምርቶችን ማገበያየቱን አስታወቀ። አንድ የመገበያያ ወንበር በ3.5 ሚሊዮን ብር ሸጧል።
በቅርቡ ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት የተቀላቀለው አኩሪ አተር ግብይት በመጋቢት ወር ብቻ የ47 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
ምርት ገበያው ለአርትስ ቲቪ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በመጋቢት ወር 21 ሺህ ቶን አኩሪ አተር በ282 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ግብይቱ 25 በመቶ ድርሻ የያዘ ነው ብሏል፡፡
በመጋቢት ወር በነበሩት 21 የግብይት ቀናት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ያወጡ ቡና፣ ሰሊጥ ፣አኩሪ አተር፣ ነጭ ቦለቄና አረንጓዴ ማሾ ግብይቶች ተካሂደዋል።
ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የሰሊጥ ግብይት በ25 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን ነጭ ቦለቄ 74 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአባልነት ወንበር በ3.5 ሚሊዮን ብር ተሽጧል፡፡ ምርት ገበያው የአባልነት ወንበሮችን ለመሸጥ ለሰባተኛ ጊዜ ባካሄደው ጨረታ እስከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድረስ ላቀረቡ ተጫራቾች የአባልነት ወንበሮችን አስተላልፏል፡፡
በጨረታው ሶስት ተጫራቾች የምርት ገበያውን የአባልነት ወንበር ለመግዛትዋጋ ያቀረቡ ሲሆን ለጨረታው የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሲሆን ዝቅተኛው 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መሆኑንም ሰምተናል፡፡