የትግራይ ክልል በቀይ ባህር ላይ መርከብ ሰጥማ ከ40 በላይ ኢትዮጵያን ህይወት በማለፉ የተሰማውን ሀዘን ገለፀ
የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በቀይ ባህር ላይ በደረሰ የመርከብ መስጠም አደጋ ከ40 የሚበልጡ ወደ ሳዑዲ አረቢያና የመን ሲያመሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ህይወት በማለፉ የተሰማውን ሀዘን ገለፀ።
የመስጠም አደጋው ከትግራይ ክልል አፅቢ ወንበርታና አካባቢው ተነስተው በቀይ ባህር ወደ የመንና ሳዑዲ ዓረቢያ ለማቅናት በጀልባ ሲጓዙ ነው የሰጠመው ተብሏል።
የአፅቢ ወንበርታ የህዝብና የመንግስት ግንኙነት ፅህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ የወይንእሸት ዘላለም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በመስጠም አደጋው ህይወታቸውን ላጡ 43 ዜጎች ቤተሰቦች ትናንት እና ዛሬ መርዶ ተነግሯል።
ቤተሰቦች እርማቸውን እንዲያወጡም በጋራ በቤተክርስቲያን የፍትሃት ስነስርዓት መከናወኑንም እና በነገው እለት ምሽት 12 ሰዓት ላይም የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት እንደሚከናወን ላፊዋ የገለፁት።
በተጨማሪም በሳዕሲዕ ፃዕዳ እምባ ወረዳ በተመሳሳይ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ አራት ወጣቶች ቤተሰቦች መርዶ መነገሩን የወረዳው የህዝብና የመንግስት ግንኙነት ፅህፈት ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል።
የክልሉ መንግስት በሀዘን መግለጫው በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጆች መፅናናትን ተመኝቷል።
በአካባቢው በህገወጥ ደላሎች ተታለው ወደ አረብ ሀገራት በሚጓዙ ወጣቶች ላይ መሰል በባህር ላይ የጀልባ መስጠም አደጋ የበርካታ ዜጎች ህይወት ማለፉን መረጃዎች ያሳያሉ።