እስካሁን ይፋዊ ስም ያልወጣለት ዘመናዊ ማረሻ በኢትጵያዉያን ተሰርቶ ተመረቀ
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሰራው ባለሞተር ማረሻ የአርሶ አደሩን ድካም ያቃልላሉ ተብሏል፡፡
የኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያን ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና የሮዳ ኢንጂነሪን ሰራተኞች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከውጭ የተገዙ ዘመናዊ ማረሻዎች ከሀገራችን ድንጋያማ መሬት ጋር ባለመስማማታቸው ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ያሉት ሚኒስትሩ ፤ይህኛው ባለሞተር ማረሻ ግን ለሀገራችን መሬት ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡
ከሞተሩ ውጪ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰራ በመሆኑ ለጥገና፤ ማሻሻያ ለማድረግና ተጨማሪ ጥቅሞችን ለመጨመር የተመቸ ነው፡፡
በቀጣይ በዚሁ ባለሞተር ማረሻ ላይ አርሶ አደሩ ተቀምጦ የሚያርስበት፤ መሬቱን ለመጎልጎል የሚያስችል፤ ምርቱን ማረሻው ላይ ለመጫን የሚያስችሉ አዳዲስ ግልጋሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ እንደሚዘምን የሮዳ ኢንጂነሪን ባለቤት አቶ አክሊሉ አባተ ተናግረዋል፡፡
ማጨድና መውቃት፤ እንዲሁም ምርት መሰብሰብ የሚችል መጎታችም በቀጣይ እንደሚሰራለት ተጠቁሟል፡፡
አርሶ አደሩ በቀላሉ ነዳጅ ማግኘት እንዲችል ከእፀዋት ተረፈ ምርት መሰራት የሚችል ማዮፊዩል እንዲጠቀምም ይደረጋል ተብሏል፡፡
ሚኒስትሩ ባለሞተር ማረሻውን አርሶ አደሮች የመግዛት አቅም ኖሯቸው እንዲጠቀሙበት ለማድረግም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ዋጋውም ከጥንድ በሬዎች መግዣ ባነሰ ዋጋ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ጥረት እንደሚደረግ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡