SportSports

ቶተንሃም እና ሊቨርፑል ወደ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ አልፈዋል

በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ የትናንት ምሽት ጨዋታዎች አስገራሚ ትዝታን ጥለው አልፈዋል፡፡

ኢቲሃድ ላይ በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የማንችስተር ሲቲ እና ቶተንሃም ሆትስፐር ጨዋታ ደስታ እና ሀዘን በቅፅበት እየተፈራረቁበት በመጨረሻም ፌሽታ ወደ ለስፐርሶች ብቻ ሁኗል፡፡

በምሽቱ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ 21 ደቂቃዎች ውስጥ በሁለቱም ቡድኖች አምስት ጎሎች ሲቆጠሩ፤ በሙሉ ጨዋታው ሰባት ጎሎች መረብ ላይ አርፈዋል፡፡  

ሲቲ በስተርሊንግ የ4ኛ ደቂቃ ግብ በድኑን ቀዳሚ ቢያደርግም፤ የስፐርስ ቁልፍ ተጫዋችነቱን እያስመሰከረ የሚገኘው ሶን ሂንግ ሚን በ7ኛውና 10ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ሲያደርግ፤ ሲቲዎች ደግሞ ከዚህ በኋላ ሶስት ግቦችን እንዲያስቆጥሩ ግድ ሆነባቸው፤ ቢሆንም በቤርናርዶ ሲልቫ የ11ኛ እና በስተርሊንግ የ21ኛ እንዲሁም በአጉዬሮ የ59ኛ ግብ ዘ ሲቲዚንስ ወደ 4 ለ 2 እንዲሸጋገሩ ሆነ፤ በዚህ ውጤት ሲቲ ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል የሚያስችለው ቢሆንም ተቀይሮ የገባው ፈርናንዶ ዮሬንቴ 73ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አገናኝቶ የቶተንሃምን የማለፍ ዕድል መንገድ አስያዘ፡፡ ጎሏ ግን መፅደቅ የቻለችው በቫር እይታ ከታገዘች በኋላ ነው፡፡

ሙሉ ጨዋታው ተጠናቆ በተደረገው ጭማሪ ሰዓት ላይ ከአጉዬሮ የተሻገረችለትን ኳስ ስተርሊንግ ወደ ግብ ቀይሮ ውሃ ሰማያዊዎቹን ቢያስፈነጥዝም፤ አጉዬሮ ከጨዋታ ውጭ በመሆኑ ጎሏ ተሸራለች፡፡

በጨዋታው ባለሜዳው ሲቲ 4 ለ 3 ቢረታም፤ በድምር ውጤት 4 ለ 4 ተለያይቶ ቶተንሃሞች ከሜዳው ውጭ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ግማሽ ፍፃሜውን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀላቅለዋል፡፡ በዚህም ከአያክስ ጋር የሚገናኙ ይሆናሉ፡፡   

በሌላኛው የተመሳሳይ ሰዓት ግጥሚያ ሊቨርፑል ወደ ፖርቱጋል አምርቶ ፖርቶን 4 ለ 1 በመርታት በአጠቃላይ ውጤት 6 ለ 1 ግማሽ ፍፃሜውን መዋሀዱን አረጋግጧል፡፡

ሳዲዮ ማኔ፣ መሀመድ ሳላህ፣ ሮቤርቶ ፊርሚኖ እና ቨርጂል ቫን ዳይክ ለቀያዮቹ ጎሎችን ከመረብ ሲያገኙ፤ ለፖርቱጋሉ ቡድን ኤደር ሚሊታዎ የማስተዛዘኛዋን ጎል አስቆጥሯል፡፡

ባርሴሎና በግማሽ ፍፃሜው ከሊቨርፑል ጋር የሚፋለም ሲሆን ከሁለት ሳምንት በኋላ ካምፕ ኑ ላይ ይገናኛሉ፡፡

 

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button
Close
Close
Close Bitnami banner
Bitnami