ኢስላማድ እና ቴህራን ሽብርተኝነትን ለመከላከል በጋራ እንሰራለን አሉ፡፡
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሀኒ ከፓኪስታን ጋር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የጋራ የድንበር ግብረ ሀይል ለማቋቋም ተስማምተናል ብለዋል፡፡
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ኢራን ገብተዋል፡፡
የካህን ጉብኝት ዋነኛ ዓላማ በኢራን ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ የፓኪስታን ክልል መሰረታቸውን ኢራን ውስጥ ያደረጉ ታጣቂዎች 14 የፀጥታ ሰዎች መግደላቸውን ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ ከኢራን ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ነው፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ካህን ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የመጀመሪያውን ጉብኝት ለማድረተግ ቴህራን ሲገቡ በኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሀኒ የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን ስለ ጋራ ግብረ ሀይሉ ግልፅ ማብራሪያ ባይሰጡም የፓኪስታን የደህንነት ሀላፊ ከኢራኑ አቻቸው ጋር በጋራ ተቀምጠው በስፋት ይመክሩበታል ብለዋል፡፡
ካህን ከፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሀኒ ጋር በተወያዩበት ወቅት በሁለቱ ሀገራት ምድር ሽብርተኝነት እንዳይኖር በትብብር እንደሚሰሩ ገልፀው ኢራን ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወገኖች ዓላማቸውን እንዲያሳኩ አንፈቅድላቸውም ብለዋል፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሀመድ ጃቫድ ዛሪፍ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ እና በባህል የተሳሰረ ነው፤ የአሁኑ የካህን ጉብኝትም የበለጠ ያጠናረዋል ነው ያሉት፡፡
መንገሻ ዓለሙ