ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኙት ሁሉም የድንበር በሮች መዘጋታቸው ተሰማ
ተዘጉ የተባሉትና አራቱ ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኙት ድንበር በሮች ዛላምበሳ-ሰርሃ ፣ራማ-ክሳድ ዒቃ፣ ሁመራ-ኦምሃጀር እና ቡሬ-ደባይ ሲማ ናቸው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ተዘጋ የተባለውን የሁመራ-ኦማሃጀር ድንበር በር ተከትሎ ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀንም የቡሬ-አሰብ ድንበርም በተመሳሳይ መዘጋቱ ተሰምቷል፡፡
የተቀሩት ሁለቱ ድንበሮች ደግሞ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት መዘጋታቸው ታውቋል።
ከኤርትራ ወገን ድንበሮቹ ለመዘጋታቸው ይፋዊ ምክንያት ባይሰጥም ፤ ይፋዊ ባልሆኑ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ኤርቲሪያን ፕሬስ እንዳስነበበው ግን ድንበሮቹ የተዘጉት በሁለቱ ሀገራት መካከል የቪዛ እና የቀረጥ ጉዳዮችን መልክ በማስያዝ በሁለቱም ወገን በእግር እና በመኪና እየተደረገ ያለውን ድንበር ማቋረጥ ለማስቆም ነው ተብሏል።
ከወራት በፊት ድንበሮቹ መከፈታቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት ዜጎች መካከል ቅጥ ባጣ መልኩ እየተካሄደ ሲሆን ገንዘብ መንዛሪዎችም ንግድ ደርቶላቸው ዶላር ወደ ናቅፋ ፣ናቅፋ ወደ ዶላር እና ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዝሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
ቢቢሲ ድንበሮቹ የተዘጉበትን ምክንያት የትግራይ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሊያ ካሳን ጠቅሶ ሲዘግብ የትግራይ ክልል ማብራሪያ እንዲሰጥበት የፌደራል መንግሥትን እየጠየቀ ነው ብሏል።