አዲስ የተቋቋመው የጉሙሩክ ፖሊስ ስራ ጀመረ
ኮንትሮባንድንና ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው የጉምሩክ ፖሊስ ስራ መጀመሩ ተገለፀ፡፡
ኮንትሮባንድን መከላከል ዋነኛ ተግባሩ መሆኑ የተነገረው ይኸው የጉሙሩክ ፖሊስ ተጠሪነቱ ለፌዴራል ፖሊስ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮንትሮባንድ ፖሊስ ዳይሬክቶሬትን ለማቋቋም የሚያስችል የስምምነት ሰነድ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና በጉሙሩክ ኮሚሽን መካከል ተፈርሟል።
በጉምሩክ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ቀደም ሲል ሌሎች ስራዎችን ደርቦ ሲሰራ የነበረው የፀጥታ መዋቅር በአሁኑ ወቅት ኮንትሮባንድን መከላከል ዋነኛ ስራው የሆነ የጉምሩክ ፖሊስ ነው ያደራጀው፡፡
የጉምሩክ ፖሊስ አደረጃጀቱ ተጠሪነቱ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሆኖ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በጋራ የስራ ስምሪት የመስጠትና ስራውን በጋራ የመገምገም አሰራር ይከተላል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጥናት ላይ በመመስረት 50 በመቶ በሚሆኑት የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ አዲሱ የጉምሩክ ፖሊስ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በቀሪዎቹ ኬላዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባ ይጠበቃል መባሉን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ሪፎርም ከጀመረ ወዲህ 1.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር እንዳዋለ የሚታወስ ነው፡፡