የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የተስተካካይ መርሀግብር ጨዋታዎች ትናንት ምሽት መካሄድ ጀምረዋል፡፡
በማውሪሲዮ ፖቼቲኖ የሚሰለጥነው ቶተንሃም ሆተስፐር በሜዳው ብራይተንን አስተናግዶ በጨዋታው የመገባደጃ ሰዓት ባስቆጠራት የክሪስቲያን ኢሪክሰን ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡ በዚህም ስፐርሶች ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዞ ለመጨረስ በሚያደርገው ጥረት ላይ ከ35 ግጥሚያዎች በሰበሰባቸው 70 ነጥቦች ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት በተደረገ ሌላ ጨዋታ ቪካሬጅ ሮድ ላይ ዋትፎርድ ከሳውዛምፕተን ተገናኝተው ሳይሸናነፉ በአንድ አቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡ ሼን ሎንግ በመጀመሪያው ደቂቃ አስቆጥሮ ቅዱሳኖችን መሪ አድርጎ ቡድኑ ጨዋታውን እስከ 90ኛው ደቂቃ ድረስ 1 ለ 0 ሲመራ ቢቆይም አንድሬ ግሬይ ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል፡፡
በዚህም ዋትፎርድ በ50 ነጥብ ደረጃውን ወደ 7ኛ ከፍ ማድረግ ሲችል፤ ሳውዛምፕተን ከወራጅ ቀጠና በስድስት ነጥብ ርቆ በ37 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የቅዱሳኖቹ ያለመውረድ ስጋት አሁንም አልተቀረፈም፡፡
ዛሬ ምሽት ሌሎች ተስተካካይ ጨዋታዎች ቀጥለው ይካሄዳሉ፡፡