የዲ. ኤፍ. ቢ ዋንጫ ወይንም የጀርመን ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ማክሰኞ እና ዕረቡ ዕለት ተካሂደዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በቮልክስፓርክ ስታዲየም አር. ቢ ላይፕዚህ ሀምቡርግን 3 ለ 1 ረትቶ ለፍፃሜ ዋንጫ ማለፍ ችሏል፡፡
ዩሱፍ ፖልሰን፣ ኢሚል ፎርስበርግ እና ቫሲሊጄ ያኒቺ በራሱ መረብ ላይ ላፕዚህን ለፍፃሜ ያበቁ ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
ትናንት ምሽት ደግሞ ዌሰር ስታዲየም ላይ ባየርን ሙኒክ ወርደር ብሬመንን 3 ለ 2 በማሸነፍ በጀርመን ዋንጫ ከላይፕዚህ ጋር እንደሚገናኝ አረጋግጧል፡፡
ባየርን በሮበርት ሌዋንዶውስኪ እና ቶማስ ሙለር ጎሎች 2 ለ 0 መምራት ቢችልም፤ ብሬመኖች በዩያ ኦሳኮ እና ሚሎት ራሽካ የ74ኛ እና 75ኛ ደቂቃ ግብ አቻ መሆን ችለዋል፡፡
80ኛው ደቂቃ ላይ ግን ኪንግስሊ ኮማን ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ በተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት በፖላንዳዊው አጥቂ ሌዋንዶውስኪ ተቆጥራ ቡድኑ አሸናፊ ሁኗል፡፡
በዚህም አር ቢ ላይፕዚህ እና ባየርን ሙኒክ ከአንድ ወር በኋላ በበርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም የዋንጫ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ፡፡
ሙኒክ ዋንጫውን ከፍ የሚያደርግ ከሆነ በእጁ ያለውን የጀርመን ዋንጫን የማንሳት ክብረወሰን በ19ኛ ስኬቱ የሚያስቀጥል ይሆናል፡፡