ለአምስት አመታት ከእይታ ተሰውሮ የቆየውና በብዙዎች ዘንድ ሞቷል ተብሎ የታመነው የኢስላማዊ ታጣቂ (አይ ኤስ) ቡድን መሪ አቡ ባክር አልባግዳዲ በቅርቡ በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል እንዳልሞተ አረጋግጧል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በስሪላንካ የፋሲካ በዓል ዕለት ለደረሰው የቦምብ ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል።
የኢስላማዊ ታጣቂ (አይ ኤስ) ቡድን መሪ አቡ ባክር አልባግዳዲ ድምጹን ካጠፋ ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክቱን ያስተላለፈው።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ በቅርቡ በባጉዝ ያጋጠማቸውን ሽንፈት ያመነ ሲሆን መልዕክቱ መቼ እንደተቀረጸ ግን እርግጠኛ መሆን አልተቻለም። ቡድኑ ግን ተንቀሳቃሽ ምስሉ በያዝነው ሚያዚያ ወር ላይ የተቀረጸ እንደሆነ አስታውቋል።
ቡድኑ ለተነጠቃቸው ይዞታዎችም የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል።
አቡ ባክር በአውሮፓውያኑ 2014 ሞሱል በተባለችው የሶሪያ ከተማ ውስጥ ሆኖ በሶሪያና ኢራቅ ላይ እስላማዊ ካሊፌት መስርቻለሁ ብሎ ካወጀ በኋላ የውሃሽታ ሆኖ ቀርቶ ነበር፡፡
አልባግዳዲ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ባስተላለፈው መልዕክት ከሁለት ሳምንት በፊት በስሪላንካ የፋሲካ በዓል ዕለት ለደረሰው የቦምብ ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን ባጉዝ ላይ ላጋጠማቸው ሽንፈት ምላሽ እንደሆነም አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም አልባግዳዲ የሚመራው ቡድን በቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ሱዳንና አልጄሪያ ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ስላለው ወታደራዊ ግንኙነትና መታወጅ ስላለበት ኢስላማዊ ጂሃድ መልዕክቱን አስተላልፏል።