የአውሮፓ ቻምዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ሌላ ጨዋታ ስፔን ላይ ሲካሄድ ባርሴሎና በኑ ካምፕ የእንግሊዙን ሊቨርፑል ያስተናዳል፡፡
በሩብ ፍፃሜው ባርሳ ሌላኛውን የእንግሊዝ ቡድን ጥሎ፤ ሊቨርፑል ደግሞ የፖርቱጋሉን ፖርቶ አሰናብቶ ነበር ወደ ግማሽ ፍፃሜው ዙር የተቀላቀሉት፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ተገናኝተው ሊቨርፑል በባለፉት አራት ከሜዳው ውጭ ጨዋታዎች ሽንፈት አያውቅም፡፡ ከእንግሊዝ ክለቦች በተሻለም ቀያዮቹ በካታላኑ ቡድን ላይ ከሜዳ ውጭ ጨዋታ ላይ ድል በማመዝገብ ስም አላቸው፡፡
ባርሴሎና ግን አሁንም ለፍፃሜው ይደርሳል ተብሎ ቀዳሚ ግምት የተሰጠው ቡድን ነው፡፡
ዛሬ ምሽት 4፡00 በሚጀምረው ጨዋታ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ጉዳት የነበራቸው ብራዚላውያኑ ሮቤርቶ ፊርሚኖ እና ፋቢንሆ ሊሰለፉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
የዘንድው የላሊጋ ውድድር ሊጠናቀቅ የሶስት ሳምንታት ጨዋታዎች ቢቀሩም ባርሴሎናዎች 26ኛ የላሊጋ ድላቸውን አስቀድመው ማሳካታቸውን ተከትሎ ከደስታ መልስ ሌላኛውን ታላቅ ክብር ለማከል እያለሙ የምሽቱን ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡
የአርጀንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ እና ሆላዳዊው ተከላካይ ቨርጂል ቫን ዳይክ ትንቅንቅ በምሽቱ ይጠበቃል፡፡
ብራዚላዊው ፊሊፕ ኮቲንሆ እና ሊዊስ ሱዋሬዝ የቀድሞ ክለባቸውን በተቃራኒ ማሊያ ይገጥማሉ፡፡