እ.አ.አ. ሰኔ 23/1894 ዓ.ም የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ የተመሰረተበትን ቀን ለመዘከር በመላው አለም በሚገኙ ሀገሮች የኦሊምፒክ ቀን ይከበራል፡፡ ይህንን የኦሊምፒክ ቀን ዘንድሮ ለየት ባለ መልኩ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለአንድ ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር የመነሻ እቅድ አቅርቦ የባለድርሻ አካላት በጥልቀት ከተወያዩ በኋላ እቅዱ እንዲዳብር የተለያዩ ግብአቶች ሰጥተዋል፡፡
የኦሊምፒክ ኮሚቴው ሚያዚያ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በቢሾፍቱ አዱላላ ሪዞርት በሀገር አቀፍ ደረጃ የኦሊምፒክ ሳምንትን ለማክበር ባዘጋጀው እቅድ ዙሪያ ትናንት በሂልተን ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡
የዘንድሮው የኦሊምፒክ ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ በመላው ሀገራችን በሚገኙ ህዝቦች በህዝባዊ ሩጫ፣ በከፍተኛ ክለቦች መካከል የእግር ኳስ ውድድር፣ሙዚቃዊ ኮንሰርት፣ የፓናል ውይይት፣ በየክልሉ እና ከተማ አስተዳደሩ ተወዳጅ የሆኑ ስፖርቶች ውድድር እና በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ይከበራል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሰው፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊርጊስ ሌሎች ኃላፈዎችን ጨምሮ የክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችና ኮሚሽነሮች፣ የከተማ ከንቲባዎችና የተለያዩ የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል፡፡
ዶ/ር ሂሩት ካሰው እንዳሉት የኦሊምፒክ ሳምንትን በመላው ሀገራችን ስናከብር ምርጥና ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ሀገራችን በአህጉር አቀፍና አለምአቀፍ ውድድሮች በበቂ ሁኔታ እንድትወከልና ስፖርት ለሰላም ያለውን ፋይዳ የምናሳይበት ሲሆን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ለሀገራችን ስፖርት እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ከኮሚቴው ጎን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችም የኦሊምፒክ ሳምንትን በክልላቸው ተጨባጭ ሁኔታን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ለማክበር በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ “የኦሊምፒክ ሳምንት ሁሉም የሰው ልጆች በሰላምና በወዳጅነት አብሮ የመኖር ባህልን የምናሳድግበት፣ ስፖርት ለሰላም መረጋገጥና ለሀገራዊ መግባባት ያለውን የማይተካ ሚና የምናረጋግጥበት፣ የሀገርን ክብርና ሞገስ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የምንችልበት፣ የህዝባችንን ከስፖርት ልማት ተጠቃሚነት ባልተቋረጠ ሁኔታ ማረጋገጥ፣በተለይ ወጣቶች በኦሊምፒክ መርሆች መሠረት የአካል፣ የአእምሮና የመንፈስ ጥንካሬዎቻቸውን በማጎልበት ህይወታቸውን በጹኑ መሰረት ላይ ጥለው ስፖርትን ለስራና ለሀብት መፍጠሪያ እና የገቢ ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ የምንሰራበት ነው፡፡”ብለዋል
ተሳታፊዎች ባለ 4 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተው በመላ ኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ሳምንትን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ተስማምተዋል::
መረጃው፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው፡፡