ዩጋንዳዊው የፖፕ ሞዚቃ አቀንቃኝ እና ፖለቲከኛ የፍርድ ሂደት መታየት ጀምሯል፡፡
በቅፅል ስሙ ቦቢ ዋይን በመባል የሚታወቀው ሮበርት ኪያጉላኒ የችሎት ውሎ በጥብቅ የፖሊስ ጥበቃ ስር በሚገኝበት እስር ቤት ሆኖ ነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተከናወነው፡፡
አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው ችሎቱ በዚህ ቴክኖሎጂ ታግዞ ክርክሩን ሲያዳምጥ በሀገሪቱ የፍትህ ስርዓት የመጀመሪያው ነው ፡፡
ፍርድ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ኪያጉላኒ ወደ ችሎት ሲመላለስ ደጋፊዎቹ ረብሻ ያነሳሉ የሚል ስጋ ስለገባው ነው፡፡
ጠበቆቹ በበኩላቸው የፍርድ ሂደቱ ተከሳሹ በግንባር ቀርቦ አለመከናወኑ ደንበኛችን የዋስትና መብቱን እንዳይጠይቅ እድሉን ያጠብበዋል ብለዋል፡፡
የዩጋንዳ ፖሊስ ቦቢ ዋይንን ያሰረው ከተከታዮቹን ጋር ሆኖ ህገ ወጥ ተቃውሞ አካሂዷል ተብሎ የተጣለበትን የቁም እስር ተላልፎ በመገኘቱ ነው፡፡
የፓርላማ አባል እና ተቃዋሚ ፖለቲከኛ የሆነው ይህ ድምፀዊ ከአሁን ቀደም እስር ቤት ገብቶ ባጋጠመው ከባድ ህመም ውጭ ሀገር ለመታከም ያቀረበው ጥያቄ በመንግስት ይሁንታን ባለማግኘቱ መጉላላት ደርሶበት ነበር፡፡
የኋላኋላ ግን ከሀገር እንዲወጣ ተፈቅዶለት ህክምናውን ተከታትሎ ተመልሷል፡፡ በወቅቱ ደጋፊዎቹ መሪያችን የታመመው በፖሊሶች ድብደባ ደርሶበት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ቦቢ ዋይን በዩጋንዳዊያን ወጣቶች ዘንድ ከሙዚቃው ባሻገር በፖለቲካ አቋሙ ከፍተኛ ድጋፍ ያለው ዘፋኝ እና ፖለቲከኛ ነው፡፡
መንገሻ ዓለሙ