በአሜሪካ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስተዋወቅ ያለመ የውይይት መድረክ ሊካሄድ ነዉ፡፡
የውይይት መድረኩ ግንቦት 7 እና 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ ነዉ የሚካሄደዉ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት፣ የንግድ ስራና ሌሎች የትብብር እድሎችን ለማስተዋወቅ ያለመ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ማቀዱን የዉጭጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ገልጿል።
ውይይቱ አሜሪካዊያን በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ በኢትዮጵያ የእድገት እና የንግድ ለውጥ አስተዋፅኦ ለማበርከት ያለመ መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በድረ-ገፁ ይፋ ባደረገው መግለጫ አስታውቋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ የንግድ ሥራ መሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ዋና ዋና የአሜሪካ ኩባንያዎች፣ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ የተሰማሩ እና የሁለቱን አገሮችን የንግድ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት ያላቸው አካላት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።