የ23ኛ ሳምንት የሊጉ መርሀግብር ግጥሚያዎች ዛሬ ሲጀመር በገዛህኝ ከተማ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሽረ አቅንቶ ከስሑል ሽረ ጋር ይጫወታል፡፡
ነገ አንዲሁ ሌላ ጨዋታ ሲከናወን ወራጅ ቀጠና የሚገኘው ደደቢት ወደ ሶዶ አምርቶ ወላይታ ድቻን ይገጥማል፡፡
ቀሪዎቹ የሳምንቱ ፍልሚያዎች ዕሁድ ሲደረጉ፤ አንድ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲሁም ሌሎቹ በክልል ስታዲየም ይከናወናሉ፡፡
ቅዱስ ጊዮጊስ በሜዳው በመጣበት ዓመት ከሊጉ ላለመሰናበት እየጣረ የሚገኘውን ደቡብ ፖሊስ 10፡00 ሰዓት ሲል ያስተናግዳል፡፡
ክልል የሚደረጉት ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9፡00 ሰዓት ሲካሄዱ፤ በሳምንቱ መረሀግብር ከሚከናወኑ ጨዋታዎች ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጨዋታ ሃዋሳ ላይ በሲዳማ ቡና እና በሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ መካከል ይከናወናል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው የነጥብ ልዩነት እና ወቅታዊ አቋም አንፃር ጨዋታውን በተሻለ ተጠባቂ ያደርገዋል፡፡
ሌላኛው ጥሩ ጨዋታ ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው ግጥሚያ ደግሞ ጎንደር ላይ ሲከናወን የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም በዩሃንስ ሳሕሌ የሚመራውን የትግራዩን ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ይገጥማል፡፡
የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ በኋላ ወደ ውጤት የተመለሰ የሚመስለው መከላካያ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማን ይጎበኛል ፤ የአምናው ሻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ በሜዳው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ይጫወታል፡፡
የጳውሎስ ጌታቸው ቡድን ባህር ዳር ከነማ በከተማው ግዙፍ ስታዲየም ከምስራቁ ድሬዳዋ ጋር ይፋለማል፡፡
የሊጉን የደረጃ ሰንጠራዥ መቐለ በ48 ነጥቦች ሲመራ ፋሲል በ43 ይከተላል፡፡
ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረ እና ደደቢት ደግሞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ