የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት እንግሊዛዊው ስቴዋርት ሃል ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁ መሆኑን ትናንት ለስፖርት ማህበሩ በፃፉት ድብዳቤ አሳውቀዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ ትናንት ከሰዓት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ አሰልጣኙ በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁበትን ደብዳቤ ተመልክቶ ጥያቂያቸውን ተቀበሎታል፡፡
አሰልጣኙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ሥራ አመራር ቦርድ ላደረገላቸው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ስራ አመራር ቦርዱም፤ አሰልጣኙ በክለቡ ቆይታቸው ወቅት ላከናወኗዋቸው ተግባራት አመስግኖ ቀጣይ ጨዋታዎችን ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ዋና አሰልጣኝ ሆነው እንዲሰሩ ሰይሟል ሲል የክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ አስታውቋል፡፡
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን በተደረጉ የ24 ሳምንታት ጉዞ አስሩን በድል ሲወጣ፣ በስምንቱ አቻ ተለያይቶ በአምስት ጨዋታዎች ላይ ሸንፈት ገጥሞታል፡፡
ሊጉ ሊጠናቀቅ የስድስት ሳምንታት እድሜ የቀሩት ሲሆን ጊዮርጊስ 39 ነጥቦችን ሰብስቦ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡