የጣሊያን ኮፓ ኢጣሊያ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 3፡ 45 ሰዓት ላይ በአታላንታ ቤርጋሞ እና ላትሲዮ መካከል ሮም ላይ በሚገኘው ስታዲዮ ኢሊምፒኮ ይካሄዳል፡፡
አታላንታ የፍሎረንሱን ፊዮረንቲና በአጠቃላይ ውጤት 5 ለ 4 ድል በማድረግ እ.አ.አ ከ1956 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍፃሜ መድረስ ሲችል፤ የዋና ከተማው ቡድን ላትሲዮ በበኩሉ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት 1 ለ 0 በመርታት ለፍፃሜ ዋንጫ በቅተዋል፡፡
በቅፅል ስማቸው እንስት ጣኦት የሚሰኘው የቤርጋሞው ቡድን በተያዘው ውድድር ዓመት በሴሪ ኤው መልካም ጊዜን እያሳለፈ ሲሆን ሊጉ ሊጠናቀቅ የሁለት ጨዋታዎች ጊዜ እየቀረው ከተከታዩ ሮማ በሶስት ነጥብ በልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ የቀጣይ ዓመት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማገኘት እየተገለ ነው፡፡
በዚህም በሴሪ ኤው 13 ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ምንም አይነት ሽንፈት ያልጎበኛቸው የጂያን ፔሮ ጋስፔሪኒ ልጆች ፤ በአምስቱ ደግሞ በተከታታይ ድል አድርገዋል፡፡ በመሆኑም የምሽቱን ግጥሚያ በድል ሊወጡ እንደሚችል እየተጠቆመ ይገኛል፡፡
በአሰልጣኝ ሲሞኔ ኢንዛጊ የሚመሩት ላትሲዮ ባለፉት አራት የውድድር ጊዜያት ውስጥ፤ በሁለቱ ለፍፃሜ ደርሰው አልተሳካላቸውም፡፡
ቢያንኮሴሊስቲዎች ወይንም ነጭና ውሃ ሰማያዊዎቹ ባለፉት ዘጠኝ ግጥሚያዎች ውስጥ በአራቱ ሽንፈት የገጠማቸው በመሆኑ እና ከቤርጋሞው ቡድን ጋር በነበራቸው የቅርብ ግንኙነት እጅ መስጠታቸው የምሽቱ ድል ወደ አታላንታ ሊያግድል እንደሚችል እየተገመተ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ባለፉት 23 ጨዋታዎች ግንኙነት ላይ በሶስቱ ብቻ በአቻ ውጤት ሲለያዩ በቀሪዎቹ ተሸናንፈዋል፡፡
በቡድን ዜናዎች ከአታላንታ ፓፑ ጎሜዝ፣ አንድሪያ ማሴዬሎ እና ጂያንሉካ ማንችኒ ሁሉም ቅዳሜ ዕለት ከጅንዋ ጋር በተካሄደው የሴሪ ኤ ግጥሚያ በቅጣት ያልነበሩ ሲሆን ለምሽቱ ጨዋታ ግን ዝግጁ ናቸው ተብሏል፡፡
በላትሲዮ በኩል ሰርጌ ሚሊንኮቪች- ሳቪች ከጉዳት መልስ ቡድኑን ሊያገለግል እንደሚችል ሲነገር ፤ ቶማስ ስትራኮሻ፣ ፓትሪች፣ ቫሎን ቤሪሻ እና ጆርዳን ሉካኩ ግን ከጨዋታው ውጭ ናቸው ተብሏል፡፡