ለጥናትና ምርምር ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠዉ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸዉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀውን የጥናትና ምርምር ሳምንት ፕሮግራም ላይ ነዉ፡፡
ፕሮግራም በይፋ ሲከፈት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም፣እንደገለጹት ከዚህ በፊት ለጥናትና ምርምምር አስፈላጊው ትኩረት ሳይደረግ እንደቆየ ገለጸዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት-ዓመታት መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በማስፋፋቱ በዚህን ሰዓት ከሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል አግኝተው በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ፕሮፌሰር ሂሩት፤ጎን ለጎን ግን ዘርፉ አስፈላጊው ትኩረት ለጥናትና ምርምር አላደረገም ብለዋል፡፡
አሁን ግን በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩ ትኩረት አግኝቶ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙና፤ ከእነዚህም የጥናትና ምርምር ጉዳዮች በዳይሬክተር ጀነራል ደረጃ እንድመራ ተደርጓል፡፡
ፕ/ር ሂሩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልምድ እና ተሞክሮ በመውሰድ በተናጠልም ሆነ በጋራ የጥናትና ምርምር ባህልን በማዳበር ዘርፉ ለአገራችን ብልጽግና ጉልህ ድርሻ እንድያበረክት እንድሰሩ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው መንግስት ጥናትና ምርምር ለአገር ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህንን በመገንዘብ ለከፍተኛ ትምህርት ትኩረት በመስጠት የማህበረሰቡን ችግሮች በጥናት እና ምርምር በጋራ እንቅረፍ የአገራችንን ብልጽግና እናረጋግጥ ብለዋል ፡፡
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ ለምርምርና ጥናት ትኩረት የሰጡ አገራት እድገታቸውን ማረጋገጥ እንደቻሉ አብራርተው ዘርፉ ካሉት ፋይዳዎች የተማረውን ሃይል ለማህበረሰቡ ያቀርባል፣ የፈጠራ ስራን ያበረታታል፣ ዴሞኪራሲያዊ አስተሳሰብ ያለው ማህበረሰብ እንድገነባ ይረዳል፣ የተሻሉ አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ በማቅረብ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡