AfricaSportSports

በአፍሪካ ዋንጫ አልጀሪያ ወደ ጥሎ ማለፉ ስታልፍ፤ ኬንያ የመጀመሪያ ጨዋታውን አሸንፋለች፡፡

በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ግጥሚያዎች እየተከናወኑ ሲሆን ምድብ B ላይ ትናንት በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካፈለች የምትገኘው ማዳጋስካር አሌክሳንድሪያ ላይ ቡሩንዲን 1 ለ 0 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሏን አስፍታለች፡፡

የማርኮ ኢላይማ ሃሪትራ ብቸኛ ጎል ደግሞ በምድቡ አራት ነጥብ ላይ እንድትደርስ አግዟል፡፡ በቀጣይ ከምድቡ ማለፏን ለማረጋገጥ አስቀድማ ጥሎ ማለፉን ከተቀላቀለችው ናይጀሪያ ጋር ብርቱ ፉክክር ይኖራቸዋል፡፡

ምድብ C ላይ በተጠበቀው ጨዋታ አልጀሪያ ሰኔ 30 ስታዲየም ላይ ሴኔጋልን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፉ የተሻገረችው ሶስተኛዋ ብሔራዊ ቡድን ሆናለች፡፡ ከሶፊያኔ ቤላይሊ የተሻገረችውን ኳስ መሀመድ የሱፍ ቤላይሊ ከመረብ አሳርፎ የበርሀ ቀበሮዎቹን ሁለተኛ ድል እና ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ እርግጥ ሆኗል፡፡

በጨዋታው የተጠበቁት ለማንችስተር ሲቲ የሚጫወተው አልጀሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ እና የሊቨርፑሉ ሴኔጋላዊ ኮከብ ሳዲዮ ማኔ ተቀዛቅዘው ተስተውሏል፡፡

ከምድቡ ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኬንያ እና ታንዛኒያ በዚሁ ሰኔ 30 ስታዲየም ምሽት 5፡00 ላይ ተገናኝተው የሃራምቤ ኮከቦች የውድድሩን የመጀመሪያ ድል 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አግኝተዋል፡፡

በኢማኑኤል አሙኒኬ የምትመራው ታንዛኒያ ሁለቴ የመምራት እድል ቢኖራትም ከመሸነፍ አልዳነችም፡፡

ሲሞን ምሱዋ እና ምብዋና ሳማታ ለአልጀሪያ ቢያስቆጥሩም፤ ሚካኤል ኦሉንጋ ሁለት እና ጆሃና ኦሞሎ ተጨማሪ ጎል ኬንያን አሸናፊ አድርገዋል፡፡

ምድብ D ላይ በመጀመሪያው ግጥሚያ ድል ያደረጉት ሞሮኮ እና አይቮሪ ኮስት ካይሮ ከተማ በሚገኘው አል ሳላም ስታዲየም ምሽት 2፡00 ላይ ይጫወታሉ፡፡ በሔርቬ ሬናርድ የምትሰለጥነው ሞሮኮ ናሚቢያን እንዲሁም በኢብራሂም ካማራ የምትመራው አይቮሪ ኮስት ደቡብ አፍሪካን በተመሳሳይ የ1 ለ 0 ውጤት ረትተዋል፡፡

የጨዋታው አሸናፊ የሚሆነው ብሔራዊ ቡድን ቀጣዩን ዙር ይቀላቀላል፡፡ 2015 ላይ ከአይቮሪ ኮስት ጋር የአፍሪካ ዋንጫን ያሳኩት ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ሔርቬ ሬናርድ የቀድሞ ስኬታማ ቡድናቸውን በተቃራኒው ይገጥማሉ፡፡

ምሽት 5፡00 ሰዓት ሲል ከምድቡ ውድድሩን በሽንፈት የጀመሩት ደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያ ከአፍሪካ ዋንጫው በጊዜ ላለመሰናበት እያለሙ ይፎካከራሉ፡፡

በምድብ E ደግሞ 11፡30 ሲል ቱኒዚያ እና ማሊ በሱዊዝ ስታዲየም ይጫወታሉ፡፡ ማሊ በመጀመሪያው ጨዋታ ማውሪታኒያን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ስትረታ፤ ቱኒዚያ እና አንጎላ በአንድ አቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል፡፡

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button
Close
Close
Close Bitnami banner
Bitnami