አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 ቅጣቱ የተጣለዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ሰባት ወራት በመርካቶ ባደረገው ቁጥጥር ነዉ፡፡ቅጣት የተጣለባቸዉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችን በአግባቡ ባልተጠቀሙና ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ በተገኙ አንድ ሺ 71 ግብር ከፋዮች ላይ ሲሆን፡ከ 40 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዳደራዊ ቅጣት መጣሉን አስዉቋል።
በቢሮው የህግ ተገዥነት ዘርፍ፤ የታክስ መረጃና የሽያጭ መመዝገቢያ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ነጋሽ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ 592 ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ በመገኝታቸው 29 ሚሊዮን 600 ሺ ብር አስተዳደራዊ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡ ሌሎች 479 ግብር ከፋዮች ደግሞ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችን በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ነዉ የ11 ሚሊዮን 90 ሺ ብር አስተዳደራዊ ቅጣት የተጣላባቸዉ፡፡
በመርካቶ በ29ሺ 369 ንግድ ቤቶች ላይ በተደረገው ፍተሻ አንድ ሺ 71 ግብር ከፋዮች የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችን በአግባቡ ባለመጠቀማቸውና ያለደረሰኝ ግብይት እደሚፈፅሙ ታዉቋል።