ለሕክምና ባለሙያዎች የሕይወት መድህን ዋስትና ሊገባላቸው ነው::
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5፣ 2012 በኢትዮጵያ የኮሮና ህሙማንን በቅርብ ለሚከታተሉ የሕክምና ባለሙያዎች የሕይወት መድህን ዋስትና ከኢትዮጵያ መድህን ኢንሹራንስ ኤጀንሲ ጋር በሚደረግ ስምምነት ሊገባላቸው እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በፌስቡክ የቀጥታ ስርጭት ባደረጉት ውይይት በተለይ የኮሮና ህሙማንን በቅርበት ለሚከታተሉ የሕክምና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ቢያዙ እና በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸው ቢያልፍ የሕይወት መድህን ዋስትና ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል።የሕክምና ባለሙያዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የመኖሪያ ቤት፣ ስልጠና እና የመከላከያ አልባሳትን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ነው ሚንስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡ዶ/ር ሊያ የጤና ባለሙያዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።