በኢትዮጵያ ተጨማሪ 8 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2012 በኢትዮጵያ ተጨማሪ ስምንት ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ ባለፉት 24 ሰዓታት 447 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው በስምንቱ ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።ቫይረሱ ከተገኘባቸው ግለሰቦች ውስጥ አምስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ሶስቱ የ62 ዓመት ወንድ እንዲሁም የ16 እና የ14 ዓመት እድሜ ሴቶች ሲሆኑ፥ የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የ40 ዓመቱ ኢትዮጵያዊም የጉዞ ታሪክ የሌለው እና የስራው ባህሪ ተጋላጭነት ያለው መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ፥ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ደግሞ የጉዞ ታሪክ ያለው እና ከአሜሪካ በመምጣት በለይቶ ማቆያ ውስጥ የቆየ ነው።ቀሪዎቹ ማለትም የ20 ዓመት ኤርትራዊ እንዲሁም የ37 ዓመት ሶማሊያዊ እና የ38 ዓመት የብሪታኒያ ዜግነት ያለው ሲሆኑ፥ ሶስቱም ከብሪታኒያ የመጡ እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ናቸው።ይህንንም ተከትሎ በሀገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 82 መድረሱን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።በኢትዮጵያ እስካሁን ለ4 ሺህ 557 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።