ዛሬ ምሽት በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሮማ ከ ማድሪድ የሚያደርጉት ግጥሚያ ይጠበቃል
አርትስ ስፖርት 18/03/2011
በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ አምስተኛ ግጥሚያዎች ዛሬ እና ነገ የሚከናወኑ ሲሆን ከምድብ አምስት እስከ ስምንት የሚገኙ ቡድኖች ዛሬ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ፡፡
ከምድብ አምስት በአሊያንዝ አሬና ባየርን ሙኒክ የፖርቱጋሉን ቤኔፊካ ያስተናግዳል፡፡ ኤኢኬ አቴንስ ደግሞ ከ አያክስ ጋር ይጫወታል፡፡ ምድቡን ሙኒክ በ10 ነጥብ ሲመራ አያክስ በ8 ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡ ሙኒክ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ አንድ ነጥብ ይበቃዋል፡፡
በምድብ ስድስት የእንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ ወደ ፈረንሳይ አቅንቶ ከ ሊዮን ጋር ይፋለማል፤ ሆፈንየም ከ ሻክታር ዶኔስክ ይጫወታሉ፡፡ ማ.ሲቲ ምድቡን በ9 ነጥብ ሲመራ ሊዮን በ6 ነጥብ ይከተላል፡፡ እስካሁን ከምድቡ ወደ ተከታዩ ዙር ማንም ማለፍ አልቻለም፡፡
በምሽቱ በሰባተኛው ምድብ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ጨዋታ በሪያል ማድሪድና ሮማ መካከል ሮም ኦሎምፒክ ላይ ይፋለማሉ፡፡ ሲኤስኬኤ ሞስኮው ከ ቪክቶሪያ ፕለዘን የሚጫወቱ ይሆናል፡፡ በምድቡ ማድሪድና ሮማ 9 ነጥቦችን በመሰብሰብ ወደ ጥሎ ማለፉ የመግባት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡
በመጨረሻው ምድብ በአሊያንዝ ስታዲየም ዩቬንቱስ ቫሌንሲያን ያስተናግዳል፤ በኦልድ ትራፎርድ ደግሞ ማንችስተር ዩናይትድ ከ ሲውዘርላንዱ ያንግ ቦይስ ጋር ይፋለማሉ፡፡ በምድቡ አሮጊቷ በ9 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ስትገኝ ቀያይ ሰይጣኖቹ በ7 ነጥብ ይከተላሉ፡፡
በምሽቱ ኤኢኬ አቴንስ ከ አያክስ እና ሞስኮው ከ ቪክቶሪያ ፕለዘን ከምሽቱ 2፡55 ሲጫወቱ ሌሎቹ በተመሳሳይ ምሽት 5፡00 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡