አርትስ 08/04/2011
የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በእርስበርስ ጦርነት የምትታመሰውን ሶሪያን በመጎብኘት የመጀመሪያው የአረብ ሊግ መሪ ሆነዋል፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ሶሪያ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ የአሳድ መንግስትና ተቃዋሚዎች ወደ ጦርነት ከገቡ ወዲህ በአንድም የዓረብ ሊግ ሀገር ተወካይ ተጎብኝታ አታውቅም፡፡
አልበሽር ደማስቆ እንደገቡ ከሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ በሚችሉባቸዉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል ተብሏል፡፡
አልበሽር ሳና ለተባለው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን እንደተናገሩት ሶሪያን ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሱዳን የቻለችውን ሁሉ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ሶሪያ በፍጥነት ከጦርነት አገግማ በቀጠናው ያላትን የሰላም ሚና እንደምታስጠብቅ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
አሳድ በበኩላቸው አልበሽርን ሀገራቸውን ስለጎበኙላቸው አመስግነው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ጉብኝቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሶሪያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 ጦርነት ውስጥ ከገባች ጀምሮ ከ22ቱ የአረብ ሊግ ሀገራት አንድትገለል ተደርጋለች፡፡
በሶሪያ በተረደገው የእርስበርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ሚሊዮኖች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡