በቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሞት ታላላቅ ሰዎችና አምባሳደሮች ሃዘናቸውን ገልጸዋል
አርትስ 10/04 /2011
በመኖሪያ ቤታቸው በተዘጋጀው የሃዘን መግለጫ መዝገብ ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የሃዘን መግለጫ ላይ መዝገብ ላይ መልዕክቶቻቸወን ያሰፈሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አራተኛው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዮስን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶችና ወዳጅ ቤተሰቦቻቸው ናቸው።
በወጣው የቀብር ስነ ስርዓት መርሃ ግብር መሰረት በዛሬው እለት በፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ቤት በተካሄደው የሃዘን መግለጫ ስነስርዓት ላይ የአገራት አምባሳደሮችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በቀድሞው ፕሬዚዳንት ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ በተለምዶ የድሮው ጦር ኃይሎች በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት በመገኘት በተካሄደው የሃዘን መግለጫ ላይ የቻይና፣ ከፖርቹጋል፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ አሜሪካ፣ ራሽያ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ህንድ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኒጀር፣ ፊንላንድና ፍልስጤምን ጨምሮ በርካታ አምባሳደሮች ሀዘናቸውን የተመለከተ መልዕክት አስፍረዋል።
አምባሳደሮቹ በዚሁ መልዕክታቸው ፕሬዚዳንቱ ከወጣትነት ጀምሮ ህዝባቸውንና አገራቸውን በማገልገል የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የተወጡ፤ ለአገራቸውና ህዝባቸው ፍፁም ተቆርቋሪ መሪ እንደነበሩ አመልክተዋል።
በተለያዩ አገራት ተመድበው የሚሰሩ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችም በተመሳሳይ ሀዘናቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።