አርትስ 12/04/2011
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትናንት በወቅታዊ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ፥ ኦሮሞ እና ኦሮሚያ በሰላም የሚኖሩ ናቸው፤ በኦሮሚያ ውስጥም ይሁን እንደ ሀገር ኦሮሞ በገዳ ስርዓት ፍልስፍና መሰረት ለሁሉም እኩል የሆነች፣ ሰላም፣ ልማት እና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ሀገር ለመፍጠር በትግልም ይሁን በሀሳብ በማሸነፍ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ በአሁኑ ወቅት ለክልሉም ይሁን እንደ ሀገር የሰላምና እኩልነት ጮራ እንዲፈነጥቅ የማድረግ ጉዞ ጀምሯል ነው ያለው።
በዚህም በሀገሪቱ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የመጠላላት እና የአፈሙዝ ፖለቲካ በውይይት እና ሰላማዊ መንገድ እንዲቀየር ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ገልጿል።
አዲፒ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ ከጎኑ አሰልፎ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገር የቻለው በትጥቅ እና በተኩስ ሳይሆን የኦሮሞነትን እሴት እና ሰላምን አማራጭ አድርጎ በመጓዙ ብቻ ነው ብሏል።
የሴራ እና የተንኮል መንገድ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲዘጋ እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ በተለይም በኦሮሞ መካከል የሚደረግ የትጥቅ ትግል አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለው መሆኑን በማመን ኦሮሚያ የሰላም እና የልማት ምድር ሆና በሆደ ሰፊነት ሁሉን አቅፋ እንደምትኖር በተግባር ማሳየቱንም መግለጫው አትቷል።
ማንኛውም የፖለቲካ ፉክክር በአፈ ሙዝ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ እንዲጓዝ የሰላም በር ተከፍቷል ያለው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፥ ሀገርን የዘረፈ እና በወንጀል የተነከረ ደግሞ በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስቷል።
በተለይም እውን የሆነው የህዝቡ ፖለቲካዊ መብት በኢኮኖሚው ዘርፍም እንዲደገም እንዲሁም ለህዝቡ የተገባው ቃል አንድ በአንድ ተቆጥሮ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ እና ታላላቅ ተስፋዎች እየታዩ መሆኑንና ህዝቡም እየተገኘ ያለውን ድል ማጣጣም ጀምሯል ብሏል።
ኦዲፒ የኦሮሞን ትግል ወደ ቀጣይ ምእራፍ ማሻገር ብቻ ሳይሆን፥ ኦሮሞ በኢኮኖሚው ዘርፍም ስኬታማ ሆኖ ልማት እንዲስፋፋ፣ ሁሉም የኦሮሞ ሀብት ወደ ኢኮኖሚ እንዲሸጋገር እንዲሁም መሃይምነት ጠፍቶ የኦሮሞ ምሁራን የክልሉን ሀብት በእውቀት እና በችሎታ በመምራት ኦሮሞ በኢኮኖሚ ዘርፍም ነፃ እንዲወጣ ለማድረግ የተገባውን ቃል በተግባር ለመለወጥ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።
የኦሮሞ ህዝብ እና ወጣቱ የሚያነሳቸውን የኦኮኖሚ ጥያቄዎች ለመመለስ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ያስታወቀው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ ኦዲፒ ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች አንድ በአንድ ለመመለስ በድጋሚ ቃል ይገባል ብሏል።
በእጃችን የገባውን ድል በመንከባከብ ከዳር እስከ ዳር በፖለቲካ ነፃ የወጣውን ህዝብ በኢኮኖሚም ነፃ ለማውጣት እየተሰራ ባለበት ወቅት በሰላማዊ መንገድ ትልግ ለማድረግ የተገባው ቃል ፈርሶ ኢዲፒ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እያሳየ ያለውን ትእግስት እንደ ፍራቻ በመመልከት ትናንት ሲዘርፉ፣ ሲያሰቃዩ እና ከስልጣን ላይ የተባረሩ ከህዝቡ በዘረፉት ገንዘብ ተላላኪዎችን በመግዛት ኦሮሚያን እና ኦሮሞን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጠቅሷል።
የህዝቡ ሰላም እንዲደፈርስ፣ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ እና ስጋት እንዲሰማው፣ የማህበረሰቡን ችግሮች የሚቀርፉ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ እንዲሁም ለህዝቡ የተገባው ቃል እንዳይሳካ የውስጥ እና የውጭ የጥፋት ሀይሎች ኦሮሞ ሀገር መምራት አይችልም በሚል ጋብቻ ፈፅመው ሴራ ሸርበው ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑን ኮሚቴው ገልጿል።
አሁን የተገኘው ድል በአፈሙዝ፣ እርስ በእርስ በመደነቃቀፍ እና ለጠላት መሳሪያ በመሆን አልመጣም ያለው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፥ ድሉ የተገኘው በትእግስት እና በበሰለ የኦሮሞነት ፍልስፍና እንዲሁም የመደማመጥ እና አንድነት መሆኑን አንስቷል፤ ዛሬም ቢሆን ይህን መንገድ ከማጠናከር ውጭ እርስ በእርስ መዋጋት እና መታኮስ አንዱ አንዱን ከሰበረ እንጂ ወደ ቀጣይ ምእራፍ አያሻግረንም ብሏል።
ዛሬም ጠላቶች በሸረቡልን ሴራ በቂ እውቀት የሌለው የእኛው ሰው ደቦ በመውጣት በሰላማዊ ህዝብ ላይ ጭካኔ በተሞላበት የሽብር ጥቃት በፈንጂ ህይወታቸው እያለፈ፣ ሴቶች እየተደፈሩ፣ ንብረት እየወደመ እና የህዝቡ የመንቀሳቀስ መብት እየተገደበ ነው፤ ሰላም ይቅደም በማለት ሲሰሩ የነበሩ የኦዲፒ አመራሮች እና የህዝብ ጋሻ የሆነው የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትም በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እያለፈ ነው ብሏል።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም በዚህ መንገድ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
በክልሉ ላይ በተቃጣው ሴራም የህግ የበላይነት እንዳይኖር፣ የህዝቡ የመንቀሳቀስ መብት እንዲገደብ እየሆነ ነው በተለይም በምእራብ ኦሮሚያ ትምህርት እንዲቋረጥ በማድረግ የአካባቢው ነዋሪዎች መሃይምነት ውስጥ እንዲቆዩ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነውም ብሏል።
የግብይት ሁኔታው ሙሉ በሙሉ በመቆሙም ባለሀብቶች የሚሰሩት የልማት ስራ በመቋረጡም ከባንክ የተበደሩትን ብድር መመለስ እያቃተቸው ንብረታቸው እየተወረሰ መሆኑንም አስታውቋል።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለህዝቡ አገልግሎት እንዳይሰጡ በመዝጋት፣ የጦር መሳሪያ በመዝረፍ፣ ህግ ባለበት ሀገር አመራር ደብድቦ ማባረር፣ መዝረፍ እና መግደል እንዲሁም ከባንክ ቤት ገንዘብ በመዝረፍ በአጠቃላይ በክልሉ ያለውን እንቅሰቃሴ የማደናቀፍ ስራ መሰራቱንም ነው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የገለፀው።
እኛ ከተጋጨን በመሃል ህዝቡ ይጎዳል በሚል ታግሰን ነበር ያለው ኮሚቴው፥ ከዚህ በላይ ግን ጥፋቱ ከቀጠለ የህዝብ እልቂት እና የሀገር መበተንን ያስከትላልም ነው ያለው።
የህዝቡን ህይወት እየቀጠፈ ያለው ችግር ኦሮሚያን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እና አሁን የደረስንበት የትግል ምእራፍ እንዲደናቀፍ በጠላት ተዘጋጅቶ የተቃጣ ሴራ በመሆኑ ኦዲፒ ልክ እንደ ትናንቱ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ እና ወጣቶችን ከጎኑ በማሰለፍ ብስለት እና ትዕግስት በተሞላበት መንገድ ጠላቱን በማሸነፍ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ለሰከንድ እንዳይደናቀፍና ወደ ቀጣይ ምእራፍ እንዲሸጋገር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚሰራም አንስቷል።
እንዲሁም ኦዲፒ የጥፋት ሀይሎች በተቀናጀ መንገድ የሚሸርቡትን ሴራ አክሽፎ የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ማንኛውንም አይነት እርምጃ ለመውሰድ መወሰኑንም ስራ ስፈፃሚ ኮሚቴው አስታውቋል።
ሰላም ማለት የሰው ልጅ በሰላም ወጥቶ እስከገባ ድረስ ነው፣ ፖለቲካ ማለትም የታገሉለት አካል በሰላም መኖርን እስከሚያጎናፅፍ ድረስ ነው ያለው ስራ ስፈፃሚ ኮሚቴው፥ ከዚህ ውጭ ግን አንተ አርሰህ እኔ ልዝረፍ፣ አንተ ደምተህ እኔ ልብላ፣ አንተ ሙተህ እኔ እኖራለሁ ማለት ፀሀይ የጠለቀበት ፖለቲካ ነው፤ ኦዲፒ ከህዝቡ ጋር በመሆን የህዝቡን ሰላም በማረጋገጥ የተገኘው ድል ያለምንም እንቅፋት እንዲጓዝ ለማድረግ ወስኗል ብሏል በመግለጫው።
የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የመንግስት ግዴታ መሆኑን ያነሳው ስራ ስፈፃሚ ኮሚቴው፥ ወንጀል የሚፈጽሙ እና እንዲፈፀም ሁኔታ የሚያመቻቹ አካላትን በማደን ለህግ ለማቅረብ የሚሰራው ስራ በኦዲፒ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግስት በአስቸኳይ እንዲፈጽም አቅጣጫ አስቀምጧል።
የክልሉ መንግስት ጥፋተኞችን ለህግ ለማቅረብ እርምጃ በሚወስደበት ወቅትም የኦሮሞ ህዝብ፣ ወጣቶች፣ ምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች ከጎኑ እንዲሁኑም የኦዲፒ ስራ ስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪውን አቅርቧል።
ኤፍ.ቢ.ሲ