ፌዴራል ፖሊስ ስለታገዱት የሪል ስቴት ኩባንያዎች መረጃዎች እንዲላክለት ጠየቀ
አርትስ 15/04/2011
የታገዱ የሪል ስቴት ኩባንያዎች የሚካሄድባቸው ምርመራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጠየቁ
በ28 የሪል ስቴት ኩባንያዎች ላይ ዕግድ መጣሉን ተከትሎ ፌዴራል ፖሊስ በኩባንያዎቹ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተሞችን መረጃ እንዲሰጡት በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
በደብዳቤው ላይ እንደተጠቀሰው ፌደራል ፖሊስ በሰብአዊ መብት ጥሰት እና በሙስና ወንጀል ከተጀመረው ማጣራት ጋር አያይዞ ለምርመራ ያመቸው ዘንድ መረጃውን እንደጠየቀ ገልጿል፡፡
ፌዴራል ፖሊስ የጠየቃቸው መረጃዎች የኩባንያዎቹ ባለቤቶች እነማን እንደሆኑ፣ ኩባንያዎቹ የመሬት ሊዝ የከፈሉበት ሰነድ፣ ቤት ገንብተው ያስተላለፉላቸው ግለሰቦች ዝርዝርና የተላለፈበትን ዋጋ የያዙ ሰነዶች፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሰነዶችን ነው፡፡
የሪል ስቴት ኩባንያዎች መታገድ ከተሰማ በኋላ የሪል ስቴት ገበያ ከመቀዛቀዝ አልፎ በደንበኞች ላይ ድንጋጤ መፍጠሩ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኙ ያገዳቸው የሪል ስቴት ኩባንያዎች፣ በመታገዳቸው ምክንያት የገበያ መናጋት መፈጠሩን በመጥቀስ አስተዳደሩ የጀመረውን ማጣራት ባስቀመጠው ቀነ ገደብ እንዲያጠናቅቅ ጠይቀዋል፡፡
የማጣራት ሒደቱ በፍጥነት አልቆ ሕጋዊና ሕገወጡ ተለይቶ ዘርፉ በፍጥነት ከቀውስ መውጣት አለበት በማለት፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች የማጣራት ሒደቱ እንዲፋጠን ጠይቀዋል፡፡ ሪፖርተር እንዳስነበበው፡፡