የደሴ ከተማ አስተዳደር ጥፋት ፈጽመዋል ባላቸው 15 የስራ ሃላፊዎች ላይ እርምጃ ወሰደ
አርትስ 17/04/11
አስተዳደሩ እርምጃ የወሰደባቸው ሃላፊዎች ጊዜያዊ የመሬት ሊዝን ወደ ቋሚነት በመቀየር ጥፋት በመፈጸም የተጠረጠሩ ናቸው።
የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ጫኔ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ከሰባት ወራት በፊት በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁና በተለያዩ ስራዎች ከተሰማሩ ሰባት ኢንተርፕራይዞች ውስጥ ለአንዱ በጊዜያዊነት የተሰጠውን መሬት ወደ ቋሚ ሊዝነት በመቀየራቸው ነው።
እንደምክትል ከንቲባው ገለጻ ውሳኔውን ያሳለፈው የከተማ ልማት ማኔጅመንት ኮሚቴ ህጉ ጊዜያዊ ሊዝን ወደ ቋሚነት የመቀየር ስልጣን የለውም።
በዚህ መሰረትም የደሴ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ዋና ስራ አስኪያጅን ጨምሮ በድርጊቱ ቀጥታ ተሳትፈዋል የተባሉ የስራ ሂደት አስተባባሪዎችና በስራቸው የነበሩ ባለሙያዎች ካለፈው አርብ ጀምሮ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱና ከስራ እንዲታገዱ መደረጉን ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡
“አሁን የተወሰደው ጊዜያዊ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔ በቀጣይ ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋሉ” ብለዋል።
ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ዙሪያ ችግሮች እንዳሉ መረጃዎች በመድረሱም ክፍለ ከተሞች አገልግሎቱን ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይሰጡ መደረጉንም ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡ የተጀመሩ የማጥራትና የምርመራ ስራዎች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት እስኪጀመር በትዕግስት እንዲጠብቅም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ብሏል ኢዜአ በዘገባው፡፡