የሥነ ምግባርና የጸረሙስና ኮሚሽን በሀገሪቱ የተካሄደዉ የተደራጀ ሌብነት ከአቅሜ በላይ ነበር አለ፡፡
አርትስ 19/04/2011
በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና ባለሀብቱ በቅንጅት ሲፈፀሙ የነበሩት የተደራጀ ሌብነት ከፌደራል ሥነ ምግባርና ከፀረሙስና ኮሚሽኑ አቅም በላይ እንደነበር ተገለፀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት ሙስናና የተበላሹ አሠራሮች በሀገራችን በመጨመር ላይ ነው።
የሙስና ብልሹ አሠራር በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተዋናይነት የተከወነ፣ የተደራጀ ሌብነት በመሆኑ ከሥነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽኑ አቅም በላይ ነበር ብለዋል።
ኮሚሽኑ ብቻውን የሚሠራው ነገር አለመኖሩን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ሕብረተሰቡ፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትና መንግሥት በጋራ ሆነው በመሥራት አስተዋጽዖ ካላበረከቱ ኮሚሽኑ ብቻውን የሚወጣው አለመሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በአዋጅ ሲቋቋም ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ከተገኝ የማጣራት የመመርመርና የመክሰስ መብት ነበረዉ፣ አሁን ግን ኮሚሽኑ የመጣለትን ጥቆማ በማጣራት ባገኝው መረጃ ተገቢውን ቅጣትና እርምጃ እንዲወሰድ ለሕግ አካል መረጃዎቹን የማቅረብ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነዉ ብለዋል።