የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይትና ድርድር የሚመራበት ረቂቅ ደንብ ፀደቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር በቀጣይ የሚያደርጉት ውይይትና ድርድር የሚመራበት 16 አንቀጽ ያለው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይተው ማፅደቃቸውን፣ በውይይቱ ከተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማወቅ መቻሉን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ፓርቲዎቹ ከዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት በጉዳዩ ላይ በጋራ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተገኝተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ የምርጫ ቦርድ ባቀረበው ረቂቅ ላይ ቢጨመር፣ ቢቀነስ ያሉትን ሐሳብ ሰንዝረው በስምምነት እንዳፀደቁት የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡
የአወያይን ሚናና ማንነት በተመለከተ ደግሞ በፓርቲዎቹ የሚመረጡ ገለልተኛ አወያዮች፣ የውይይትና የድርድር መድረኩን እንዲመሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የአጀንዳዎች ውሳኔን በተመለከተ በ50 + 1፣ በሁለት ሦስተኛ ድምፅና በስምምነት ይወሰኑ የሚሉ ሐሳቦች ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻ ውሳኔዎች በስምምነት ይተላለፉ የሚለው ነጥብ ላይ ከስምምነት መድረሱ ታውቋል፡፡
ፓርቲዎቹ አወያዮች እንዲሆኑ የሚፈልጓቸውን ግለሰቦች ለምርጫ ቦርድ ከላኩና አወያዮቹ ከተመረጡ በኋላ፣ ፓርቲዎቹ ለውይይትና ለድርድር በመረጧቸው 32 አጀንዳዎች ላይ ውይይትና ድርድር ይጀመራል ተብሏል፡፡