የህጻናትን ጤንነት ላይ መንከባከብ ሀገርን የማስቀጠል ዋስትና መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቷ ይህን ያሉት በኪዩር ኢትዮጵያ ሆስፒታል የ10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በተገኙበት ወቅት ነው።
ኪዩር ኢትዮጵያ ከረጂ ድርጅቶችና ከኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበር ባለፉት 10 ዓመታት ከጡንቻና ከአጥንት ችግር ጋር በተያየዘ አካል ጉዳተኛ ሆነው ለተወለዱ ህፃናት 17 ሺህ የህፃናት ቀዶ ህክምና ማድረጉን ያሳወቀ ሲሆን ፕሬዚዳንቷም በንግግራቸው የሆስፒታሉን ተግባር አድንቀዋል።
ሆስፒታሉ ህፃናቱ ከእኩዮቻቸው ጋር ትምህርት ቤት እንዲውሉ በማድረግ የማህበረሰቡን አጋርነት ማሳየቱንም ተናግረዋል።
ከ15 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት 40 በመቶ በሆኑባትና የአጥንትና የጡንቻ ችግሮች በተለመዱባት ኢትዮጵያ ኪዩር ኢትዮጵያ በህፃናት ጤና ዘርፉ ቁልፍ ሚናውን እየተወጣ ነውም ብለዋል ፕሬዚዳንቷ።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በማሳሰቢያቸው ተቋሙ የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ህፃናት ነፃ የህክምና አገልግሎት መስጠት አለበት ብለዋል።
ከተመሰረተ 10 ዓመት የሞላው ሆስፒታሉ የአካል ጉዳት ላለባቸው ህፃናት የቀዶ ህክምና እና ሌሎች ሁለገብ የህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣል ሲል ኤፍ.ቢ.ሲ ዘግቧል ፡፡