በድሬዳዋ የተፈጠረው ግጭት ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የለውም ተባለ
ጥር 12 እና 13 በድሬዳዋ ከተማ የተከሰተው የወጣቶች ጸብ ከኃይማኖት ጉዳይ ጋር ግንኙነት እንዳልነበረው የከተማዋ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ።
የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖት አባቶች ግጭቱን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ የሃይማኖት አባቶቹ እንደተናገሩት ግጭቱን የፈጠሩ አካላትም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ።
የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ-ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው እንዳሉት ግጭቱን የፈጠሩት አካላት ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በማሰብ የፈጸሙት እንጂ ከኃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል።
የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊ ሼህ ኢብራሂም ኢማም አህመድ በበኩላቸው በከተማው የኃይማኖት ተቋማት ለሰላም መስፈን፤ ለኃይማኖታዊ በዓላት መድመቅና ማማር በጋራ የሚሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ጥፋት የተሳተፉ ሰዎች ታድነው ለህግ መቅረብ አለባቸው፤ በግርግር ውስጥ ዘረፋ የፈፀሙ ሰዎችም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ወጣቶች መቼም ቢሆን ባልተረጋገጠ አሉባልታ ከመመራት ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ችግሩ የተቀሰቀሰው ታቦት በሚሸኝበት ወቅት ድንጋይ በመወርወሩ ነው።
በግጭቱ የሰው ህይወት አለማለፉና የከፋ ጉዳት አለማጋጠሙን የተናገሩት ሃላፊው የከተማዋ ፖሊስ ግጭቱ እንዲቀሰቀስ ያደረጉና ጥፋት ያደረሱ አካላትን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ወጣቶች እንዳሉት የተፈጠረው ድርጊት መወገዝ የሚገባውና የድሬዳዋ መገለጫ ያልሆነ ተግባር ነው።