ኢትዮጵያ ቡና እና አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ዳሮሣ መለያታቸውን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ ተናገሩ፡፡
የስንብቱን መረጃ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የፌስቡክ ገፅ ይፋ አድርጓል።
አርትስም ከክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታሁ በቀለ ጋር በነበረው የስልክ ቆይታ አሰልጣኙ እና ክለቡ መለያየታቸውን አረጋግጠው፤ ሙሉ ፍችው በመጭው ሰኞ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡
አሰልጣኙ ከዓመት በፊት ቡናን ለማሰልጠን የተስማሙ ሲሆን ቀሪ የሁለት ዓመት ኮንትራት ነበራቸው፡፡ በጎሜስ የሚመራው ቡድን በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ መልካም ውጤት ቢያስመዘግብም፤ ባለፉት አራት የሊጉ ግጥሚያዎች ግን ተከታታይ ሽንፈት ከማስተናገዱ በተጨማሪ ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ አለማሳየቱ በየሳምንቱ ስታዲየም እየታደመ ድጋፍ የሚሰጠው 12 ቁጥር ለባሹ ደጋፊ በኩል አሰልጣኙ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ነበር፡፡
ቡድኑ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር ከ15 ጨዋታዎች ስድስቱን አሸንፎ፤ በአምስቱ ሲሸነፍ በአራቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል፡፡ በደረጃ ሰንጠራዡም 8ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡
በውሉ መሰረት ቡድኑ ለተከታታይ 3 ጨዋታዎች ሽንፈት ካጋጠማቸው ሊያሰናብታቸው የሚችልበት አንቀፅ በመጠቀም አሰልጣኙ በቀጣይ ጨዋታ እንዲያስተካክሉ ተጨማሪ ዕድል ቢሰጣቸውም በድጋሚ ሽንፈትን በማስተናገዳቸው እና ሌሎች ተዛማች ምክንያቶችን ከግምት በማስገባት ውላቸው እንዲቋረጥ ሆኗል ሲል የክለቡ የፌስቡክ ገፅ አስታውቋል።
አቶ ስንታሁ በስልክ ቆይታችን ወቅት ለአርትስ እንደተናገሩት፤ ዲዲዬ ጎሜስ ከዕረፍት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ መሆኑንና፤ ክለቡ በመጭው ሳምንት ከአሰልጣኙ ጋር ፊት ለፊት ከተነጋገረ በኋላ በውሉ መሰረት እንደሚሸኛቸው ተናግረው፤ እስከዛው ድረስ ግን ተጫዋቾች በምክትል አሰልጣኞች እንደሚሰለጥኑ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች ከጎሜስ ጋር ያለውን ፍች ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አሰልጣኞች ቅጥር ፊታቸውን እንደሚያዞሩ ይጠበቃል፡፡