በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋትፎርድና ዌስት ሃም ድል ሲቀናቸው፤ ሌሎች ግጥሚያዎች ዛሬ ይከናወናሉ ።
ከኤፍ ኤ ዋንጫ ጨዋታዎች መልስ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በ27 ሳምንት መርሀግብሩ ተመልሷል፡፡
ትናንት ምሽት ሁለት ግጥሚያዎች የተከናወኑ ሲሆን በለንደን ኦሊምፒክ ስታዲየም ፉልሃምን ያስተናገደም ዌስትሃም ዩናይትድ በኽርናንዴዝ፣ ዲዮፕ እና አንቶኒዮ ግቦች 3 ለ 1 ድል አድርጓል፤ ሪያን ባብል የፉልሃምን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡
በሌላኛው ጨዋታ ደግሞ ዋትፎርድ ወደ ዌልስ አቅንቶ ካርዲፍን ሜዳው ላይ 5 ለ 1 በሆነ ውጤት ሲረመርመው፤ ጄራርድ ዴሎፉ ሀትሪክ ሰርቷል፣ ትሮይ ዴኒ ሁለቱን የድል ግቦች ከመረብ ሲያሳርፍ፤ አምበሉ ባምባ ለዌልሱ ቡድን የማስተዛዘኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ አራት ያህል ግጥሚያዎች ይከናወናሉ፡፡
በርንሌ በቱርፍ ሞር ከሰሜን ለንደኑ ቡድን ቶተንሃም ሆትስፐር ጋር ተጠባቂ ግጥሚያውን ቀን 9፡30 ሲል ያደርጋል ፤ ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ በርንማውዝ ደግሞ በቪታሊቲ ወልቭስን ያስተናግዳል፤ በተመሳሳይ ሰዓት ኒውካስትል ዩናይትድ ሴንት ጀምስ ፓርክ ላይ ከሀደርስፊልድ ጋር ይጫወታል፡፡
የዕለቱ የመጫረሻ ግጥሚያ ምሽት 2፡30 ሲል ኪንግ ፓወር ስታዲየም ላይ በሌስተር ሲቲ እና ክሪስታል ፓላስ መካከል ይከናወናል፡፡
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በነገው ዕለት በቀያዮቹ ትንቅንቅ፤ በማንችስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል መካከል ይደረጋል፤ ሌሎች ታላላቅ ክለቦችም ጨዋታቸውን ይከውናሉ፡፡
ማንችስተር ሲቲ አንድ ጨዋታ ቀደም ብሎ ተጫውቶ ሊጉን በ65 ነጥቦች ይመራል፤ ሊቨርፑል በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ አንሶ ይከተላል፡፡ ቶተንሃም በ60 ነጥብ ሶስተኛ፣ ማንችስተር ዩናይትድ በ51 አራተኛ፣ አርሰናል በ50 አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፤ ቼልሲ በተመሳሳይ 50 ነጥብ በግብ መጠን አንሶ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡