በስፔን ኮፓ ዴል ሬይ የኢል ክላሲኮ ደርቢ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይደረጋል፡፡
የካታላኑ ባርሴሎና በኮፓ ዴል ሬይ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ለማድረግ ወደ ዋና ከተማ ማድሪድ በማቅናት ከተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ ጋር በሳንቲያጎ ቤርናቤው ምሽት 5፡00 ሲል ይጫወታል፡፡
ከሳምንታት በፊት ሁለቱ ቡድኖች በንጉስ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታ ካምፕ ኑ ላይ በአንድ አቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም ሎስ ብላንኮስ ለፍፃሜ ለመብቃት ማሸነፍ አሊያ ያለግብ በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ሲጠበቅባቸው፤ ባርሳ ማሸነፍ እና ከአንድ ግብ በዘለለ ግብ በአቻ ውጤት መለያየት ይኖርበታል፤ 1 ለ 1 አቻ ውጤት ሁለቱን ቡድኖች ወደ መለያ ምት እንዲያመሩ ያስገድዳቸዋል፡፡
ባርሳ ተከታታይ ስድስተኛ የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫውን ለማሳካት፤ የዛሬ ምሽቱ የመልስ ፍልሚያ ላይ ድል የግድ ይለዋል፡፡
በማድሪድ በኩል ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ የጉዳት ዜናዎች ሲሰሙ ማርኮስ ዮሬንቴ እና ኢስኮ ከምሽቱ ፍልሚያ ውጭ ናቸው፡፡ ከካታላውያኑ አማካዩ አርቱር ሜሎ የማይኖር ይሆናል፤ ተከላካዩ ሳሙኤል ኡምቲቲ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ተብሏል፡፡
በካታላኑ ቡድን ታሪክ መስራት የማይሰለቸው አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል አንድሪያስ ሜሲ ዛሬ 40ኛ የኢል ክላሲኮ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ደግሞ 26 ጎሎችን በነጭ ለባሾቹ መረብ ላይ በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱ የግሉ ነው፡፡
ሁለቱ ተቀናቃኞች ዛሬ በኤል ክላሲኮ 274ኛ የደርቢ ግጥሚያቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡