ባርሴሎና ለኮፓ ዴል ሬይ የፍፃሜ ዋንጫ ማለፉን አረጋገጠ
ትናንት ምሽት የስፔን ኮፓ ዴል ሬይ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ግጥሚያ በሳንቲያጎ ቤርናቤው ላይ ሪያል ማደሪድ ባርሴሎና አስተናግዶ ሜዳው የ3 ለ 0 ሽንፈት ገጥሞታል፡፡
በኤል ክላሲኮ ደርቢ እንግዳውን ባርሳ አሸናፊ ያደረጉ ጎሎች ዩሯጓያዊው ሊዊስ ሱዋሬዝ በጨዋታና በፍፁም ቅጣት ምት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ፤ ቀሪዋን ራፋኤል ቫራን በራሱ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል፡፡
ሎስ ብላንኮስ በቪኒሽዬሽ ጁኒዬር ፣ ካሪም ቤንዜማ እና ሬጉይሎን ጨምሮ 14 ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም አንዱንም ወደ ግብነት መቀየር አልቻሉም፡፡
በመጪው ቅዳሜ ሁለቱ የስፔን ተቀናቃኝ ክለቦች በስፔን ላ ሊጋ ሳንቲያጎ ቤርናቤው ላይ የሚገናኙ ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተከታታይ ለሶስተኛ ጊዜ ይፋለማሉ፡፡
የካታላኑ ቡድን የደርቢውን ጨዋታ በድል ማጠናቀቁን ተከትሎ በተከታታይ ለስድስተኛ ጊዜ የኮፓ ዴል ሬይ የፍፃሜ ተፋላሚነቱን አረጋግጧል፤ የባለፉት አምስት ዓመታት ውድድሮችን በድል ማጠናቀቁም ይታወሳል፡፡
ዛሬ ሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ በእስታዲዮ ዴ ሜስቲያ ቫሌንሲያ ከ ሪያል ቤቲስ ምሽት 5፡00 ይገናኛሉ፡፡
ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያውን ጨዋታ በ2 ለ 2 አቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን በድምር ውጤት አሸናፊ የሚሆነው ቡድን ግንቦት 17/2011 በሪያል ቤቲስ ሜዳ እስታዲ ቪያማሪን ከባርሴሎና ጋር ይጫወታል፡፡