ኬንያ ዓለም አቀፍ የመምህራን ሽልማት በማሸነፍ በአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ሆነች፡፡
ኬንያ ይህን የክብር ሽልማት ያሸነፈችው በ36 ዓመቱ የሳይንስ መምህር ፒተር ታቢቺ አማካይነት ነው፡፡
ታቢቺ በስልጣኔ ወደፊት ለመጓዝ ሳይንስ ሁነኛው መንገድ ነው የሚል ፅኑ አቋም ይዞ ተማሪዎቹን በራሱ ወጭ ሲያግዝ እንደነበር በመድረኩ ተመስክሮለታል፡፡
የሂሳብ እና የፊዚክስ ትምህርቶችን አጣምሮ የሚያስተምረው ታቢቺ ድሀ ተማሪዎችን ለመርዳት ሲል 80 በመቶ የሚሆነውን የወር ደመወዙን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያውል እንደነበርም ተነግሯል፡፡
በተለይ ተሰጥኦን ማዳበር የሚያስችል “ታለንት ነርቸሪንግ” የተባለ ክለብ አቋቁሞ በሳይን ምህርት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት “ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያደረገው ጥረት መልካም ፍሬ አፍርቶለታል፡፡
በዚህ ክለብ ውስጥ ችሎታቸውን ሲያጎለብቱ ከነበሩት የታቢቺ ተማሪዎች መካከልም 60 በመቶ የሚሆኑት ለሀገር አቀፍ ውድድር ብቁ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው ታቢቺ ሽልማቱ የእኔ ሳይሆን የኬንያ ታዳጊዎች እና ወጣቶች የስራ ውጤት ስለሆነ ሀገራቸውን በማስጠራታቸው ሊኮሩ ይገባል ብሏል፡፡
መምህሩን 58 ተማሪዎች በአንድ ክፍል አንዲት ኮምፒዩተር ተጋርተው የሚማሩበት ሁኔታ ተስፋ ሳያስቆርጠው ነገሮችን ለመቀየር የተጓዘው ርቀት ነው ለዚህ ሽልማት ያበቃው፡፡
ይህ ኬንያን ብሎም አፍሪካን ያስጠራ ታታሪ መምህር ቫርኪ ፋውንዴሽ በተባለ ተቋም በተሰጠው እውቅና የአንድ ሚሊዮን ደላር ተሸላሚ ሲሆን የተቋሙ ዓለም አቀፍ አምሳደር ሆኖም ያገለግላል፡፡
ታቢቺ ከ179 ሀገራት ለውድድሩ ከተመዘገቡ 10 ሺህ እጩዎች መካከል ነው የሱ ስራ ጎልቶ በመውጣቱ ሽልማቱን ያሸነፈው፡፡ ይሄም በአፍሪካ ታሪክ ኬንያን የመጀመሪያዋ አድርጓታል፡፡
መንገሻ ዓለሙ