በ18ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ግጥሚያዎች መካከል ስድስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1 ለ 0 ውጤት ተጠናቅቀዋል፡፡
ትናንት በርካታ ጨዋታዎች ሲከናወኑ በሳምንቱ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው ግጥሚያ ጎንደር ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ ሲደረግ ፋሲል ከነማ እንግዳውን መቐለ 70 እንደርታ 1 ለ 0 ረትቷል፡፡
የአፄዎቹ የድል ግብ በዓለምብርሃን ይግዛው አማካኝነት ስትቆጠር ቡድኑ በደረጃ ሰንጠራዡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡
ባህር ዳር ላይ የተገናኙት ባህር ዳር ከነማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታው በባለሜዳዎቹ የጣናው ሞገድ 1 ለ 0 ውጤት ተጠንቅቋል፡፡ ዜናው ፈረደ የግቧ ባለቤት ነው፡፡
ወደ ጅማ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በማማዱ ሲዲቤ ግብ ጅማ አባ ጅፋር 1 ለ 0 በመርታት ደረጃውን ወደ ስድስተኛ ደረጃ አሳድጓል፡፡
በትግራይ ስታዲየም ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና በአማኑኤል ዩሃንስ ብቸኛ ጎል ድል አድርጓ ወደ ድል መመለስ ችሏል፡፡
አዳማ ላይ የተካሄደውን ጨዋታ ባለሜዳው የአዳማ ከተማ ቡድን የትግራዩን ስሑል ሽረ በ4 ለ 1 ውጤት አሸንፏል፡፡
መከላከያ ከድሬዳዋ ከድሬዳዋ ጋር በ1 ለ 1 አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
ቅዳሜ ዕለት በብቸኝነት በተደረገ ጨዋታ ደደቢት በትግራይ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስን 1 ለ 0 በመርታት የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡
ፕሪምየር ሊጉ በመቐለ 70 እንደርታ 39 ነጥቦች ይመራል፤ ፋሲል ከነማ በ32 ተከታይ ነው፤ ሲዳማ ቡና በ31 ሶስተኛ ደረጃ ሲገኝ ቅዱስ ጊዮርጊሰወ በ29 ነጥቦች አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረ እና ደደቢት ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው፡፡