የጤና ሚኒስቴር ለተፈናቃዮች በጤና ባለሙያዎች የሚደረገው ድጋፍና ተጠናክሮ ቀጥሏል አለ፡፡
የጤና ሚኒስቴር በጌዲዮ ዞን ተፈናቃዮች ድጋፍ የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች፡ የተለያዩ መድሃኒቶች እና ሌሎች ግበአቶችን ወደ ስፍራው ከመላክ በተጨማሪ በጤና ባለሙያዎች የሚደረጉ የተለያዩ የህክምና ድጋፍና ክትትል ስራዎች መቀጠላቸውን ሚኒስቴሩ ለአርትስ በላከዉ መግለጫ አስታዉቋል፡፡
ቁጥራቸው 22 ሺህ 895 የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ከምግብ ዕጥረት ጋር ተያይዞ የገጠሟቸውን የጤና እክሎች በምርመራ በመለየት ተገቢውን ምርመራና ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
እንዲሁም በተፈናቃዮቹ የተለያዩ መጠለያዎች በተደረጉ ምርመራዎች የተለያዩ የጤና እክል ያጋጠማቸው 29,823 ሰዎች ተለይተው ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
ከአሁን ቀደም ወደ ስፍራው ካቀኑት ባለሙያዎች በተጨማሪ ባሳለፍነው ሳምንት 11 የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችም ለተለያዩ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ችግር የተጋለጡ ሰዎች የድጋፍና ክትትል ስራ እንዲያከናውኑ የተሰማሩ መሆኑንም ሰምተናል፡፡
ከአሁን በፊት 15 ሀኪሞች፣ 36 ነርሶች፣ 5 የአካባቢ ጤና ባለሙያዎች እና 5 የኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች እንዲሁም ከ121 በላይ የጤና ባለሙያዎች ወደ ስፍራው ማቅናታቸውንና የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ቅኝቶችና ዳሰሳዎችን ከማድረግ በተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን በመግለጫዉ ተጠቅሷል፡፡