የ2018/19 የዩሮፓ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በተመሳሳይ ምሽት 4: 00 ሰዓት ላይ ይካሄዳሉ፡፡
በምሽቱ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል አርሰናል ኤመሬትስ ስታዲየም ላይ የጣሊያኑን ናፖሊ የሚያስተናግድበት ግጥሚያ በጉጉት ተጠባቂ ነው፡፡
በቡድን ዜናዎች በሁሉም ውድድሮች 22 ጎሎችን ማበርከት የቻለው ፔር ኤምሪክ ኦባማያንግ ከፕሪምየር ሊግ ተቀይሮ መግባት መልስ ቅድሚያ የመሰለፍ ዕድል ያገኛል ተብሏል፡፡
የመድፈኞቹ አምበል ሎረንት ኮሴዬልኒ እና አማካዩ ግራኒት ዣካ ከቡድኑ ጋር ልምምድ የጀመሩ ሲሆን የሁለቱ ተጫዋቾች የመሰለፍ ጉዳይ ለመወሰን ኡናይ ኢመሪ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ይጠበቃሉ፡፡
በናፖሊ በኩል አጥቂዎቹ ሎሬንዞ ኢንሲኜ እና ሲሞኔ ቨርዲ ከጉዳት መልስ የቡድኑ ስብስብ ውስጥ ተካትተዋል፡፡
ሌላኛው የእንግሊዝ ክለብ ቼልሲ ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ተጉዞ ስላቪያ ፕራሃን ኤደን አሬና ላይ የሚገጥም ሆናል፡፡
ኤደን ሀዛርድ ድካም ላይ ስለሆነ ዕረፍት ተሰጥቶታል ሲሉ አሰልጣኝ ማውሪዚዮ ሳሪ አስታውቀዋል፡፡
ይህ ግጥሚያ በስላቪያ ፕራሃ እና ቼልሲ መካከል የሚደረግ የመጀመሪያ ፍልሚያ ነው፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ሁለቱ የስፔን ክለቦች ቪያሪያል እና ቫሌንሲያ በእስታዲዮ ዳ ላ ሴራሚካ ሲጫወቱ፤ የፖርቱጋሉ ቤንፊካ በእስታዲዮ ዳ ሉዝ የጀርመኑን አይንትራክት ፍራንክፉርት ጋር ይጫወታሉ፡፡